በናይጄሪያው ግሎ ኩባንያ ስፖንሰር አድራጊነት በጥር 2017 የሚደረገው የካፍ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሶስት የመጨረሻ ዕጩዎች ዛሬ ታውቀዋል፡፡ ሪያድ ማህሬዝ፣ ፔየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ እና ሰይዶ ማኔ ለዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነት ይፎካከራሉ፡፡
በመጨሻዎቹ አምስት ውስጥ መግባት የቻሉት ግብፃዊው መሃመድ ሳላህ እና አልጄሪያዊው አጥቂ ኢስላም ስሊማኒ የመጨረሻ ሶስቱ ውስጥ ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ አልጄሪያዊው ማህሬዝ የቢቢሲ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን ያሳካ ሲሆን የካፉንም ሽልማት እንደሚያሸንፍ ተገምቷል፡፡ ማህሬዝ ክለቡ ሌስተር ሲቲ የእንግሊዝ ሻምፒዮን ሲሆን ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ለበረሃ ቀበሮዎቹም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ የ2015 የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ጋቦናዊው ኦባሚያንግ በግሉ ለክለቡ ቦሪሺያ ዶርትሙንድ እና ለሃገሩ ግቦችን ሲያመርት ቆይቷል፡፡ ማኔ በበኩሉ ለሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን ዳግም መነነሳሳት ወሳኝ ሚናን የተጫወተ ሲሆን በሳውዝሃምፕተን እና ሊቨርፑል ብቃቱን እያስመሰከረ ይገኛል፡፡
ሶስቱ ተጫዋቾች የተመረጡት ከብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ወይም የቴክኒክ ዳይሬክተሮች፣ የሚዲያ ኮሚቴ፣ የቴክኒክ እና እግርኳስ ኮሚቴ ከኤክስፐርት የሚዲያ ፓናል አባላት በተሰበሰበው ድምፅ መሆኑን የኮንፌድሬሽኑ ድህረ-ገፅ ካፍኦንላይን ጠቅሷል፡፡
በአፍሪካ ለሚጫወቱ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን ለማግኘት ዩጋንዳዊው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎ፣ የዚምባቡዌው ካማ ቢሊያት እና የዛማቢያው አማካይ ሬንፎርድ ካላባ ተፋጠዋል፡፡
የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች
ፔየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ (ጋቦን/ቦሪሺያ ዶርትሙንድ)
ሪያድ ማህሬዝ (አልጄሪያ/ሌስተር ሲቲ)
ሳድዮ ማኔ (ሴኔጋል/ሊቨርፑል)
በአፍሪካ የሚጫወት የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች
ዴኒስ ኦኒያንጎ (ዩጋንዳ/ማሜሎዲ ሰንዳውንስ)
ሬንፎርድ ካላባ (ዛምቢያ/ቲፒ ማዜምቤ)
ካማ ቢሊያት (ዚምባቡዌ/ማሜሎዲ ሰንዳውንስ)