“ጨዋታው የመጣው ለእኛ በጣም በጥሩ ጊዜ ነው” ኒቦሳ ቩሴቪች

ኢትዮጵያ ቡና የከተማ ተቀናቃኙ ቅዱስ ጊዮርጊስን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታ ያስተናግዳል፡፡ ሰርቢያዊው የክለቡ አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሴቪችም የደርቢውን ጨዋታ በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

“ይህ የሃገሪቱ ትልቅ ጨዋታ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ (ለሰርቢያ) ብሄራዊ ቡድን እና ፓርቲዛን ቤልግሬድ በ60 እና 70ሺ ህዝብ ፊት መጫወቴ የትልቅ ጨዋታን ትርጉም እንድረዳ ያደርገኛል፡፡ ጨዋታው ለተጫዋቾቹ ጥሩ መነሳሳት ይሆናቸዋል፡፡ ጨዋታው የመጣው ለእኛ በጣም በጥሩ ጊዜ ነው፡፡ ጥሩ ጨዋታ እና ያማረ ውጤት ማግኘት ከቻልን ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡ ሶስት ነጥብ ካገኘን 10 ነጥብ ነው የምንገባው፡፡ ገና ብዙ ነጥቦች ስለሚቀሩ ከአሁኑ ነጥብ ማግኘት አለብን፡፡ የዚህ ሃገር ትልቁ ደርቢ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለዚህም ተጫዋቾቼ በሚገባ ተዘጋጅተዋል፡፡”

አሰልጣኝ ቩሴቪች የክለባቸውን የግብ ማግባት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተው መስራት ላይ እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡ “እንደመለከታችሁት ሁሌም በልምምድ ወቅት 30 እና 25 ደቂቃዎችን የግብ ማግባት ችግር የሚቀርፍልንን ልምምድ ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡ በሰባቱም ጨዋታዎቻችን ብዙ የግብ ማግባት እድሎችን አምክነናል፡፡ ግቦችን አስቆጥረን ቢሆን ኖሮ ምናልባትም የሊጉ አናት ላይ እንቀመጥ ነበር፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ድሬዳዋን ስንገጥም ብዙ የግብ እድሎችን ፈጥረን መጠቀም አልቻልንም፡፡ አንዳንዶቹ እድሎች ከፍፁም ቅጣት ምት ራሱ የቀለሉ ነበሩ፡፡ ሁሌም እንደምናገረው ይህ የእኔ ስህተት ነው፡፡ ከአሁን በኃላ በሚኖረን ጨዋታዎች ነጥቦች ስለሚያስፈልጉን ግቦች እናስቆጥራለን ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡”

በጋናው አክራ ሃርትስ ኦፍ ኦክ የሰሩት አሰልጣኙ የጋናን ታላቁ ደርቢ (አሻንቲ ኮቶኮ ከአክራ ሃርትስ ኦፍ ኦክ) ከኢትዮጵያ ጋር አነፃፅረዋል፡፡ “በኢትዮጵያ ቆይታዬ ይህ የመጀመሪያ የደርቢ ጨዋታዬ ነው፡፡ የሃርት ኦፍ ኦክ እና አሻንቲ ኮቶኮ የደርቢ ጨዋታ ከተመለከትክ ከ70ሺህ-75ሺህ ህዝብ በስታዲየም ተገኝቶ ይከታተለዋል፡፡ አሁን ላለው ጨዋታ ምናልባት 30ሺህ ሰው ቢገኝ ነው፡፡ ይህ አንዱ ልዩነት ነው፡፡”

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በውጤት መጥፋት ምክንያት አሰልጣኙ እና ተጫዋቾች ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ይህንን የተረዱት አሰልጣኝ ቩሴቪች የተሻለ ውጤት አምጥተው ደጋፊዎቻቸው ማስደሰት አላማቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“እኔ ለደጋፊዎቻችን መናገር የምፈልገው ኢትዮጵያ ቡና ለጨዋታው ተዘጋጅቷል፡፡ ያለንን ሁሉንም ነገር ለመስጠት በጣም ተዘጋጅተናል፡፡ ሶስት ወሳኝ ተጫዋቾቼ ጉዳት ላይ ናቸው፡፡ አሁን ላይ በዚህ ምክንያት መናደድ አልችልም፡፡ በቀሩን ቀናት ባሉን ተጫዋቾች ጥሩ ነገር ለመስራት እና ከሰባት ጨዋታ በኃላ ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት እንጫወታልን፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *