የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን ዕሁድ በሸገር ደርቢ ይገጥማል፡፡ የፈረሰኞቹ ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ማርቲነስ ኤግናተስ ኖይ ስለቡድናቸው ዝግጅት፣ ስለጨዋታው እና ተያያዥ ጉዳዮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ስለዝግጅት
“በእኛ በኩል ለጨዋታው ያለን ዝግጅት ጥሩ ነው፡፡ ተጫዋቾቼ በጥሩ መነቃቃት ላይ ነው የሚገኙት፡፡ በየሳምንቱ ጠንካራ ልምምድ ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡ አስቀድሜ ከውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ጀምሮ እንደተናገርኩት ከፊታችን ብዙ ጨዋታዎች አሉብን፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ፣ የጥሎ ማለፍ እና የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች አሉብን፡፡ ሁሉንም ጨዋታዎች በትኩረት ነው የምናየው፡፡ ከማንም ጋር አንቀልድም ፤ ተጋጣሚዎቻችን እናከብራለን፡፡ የኢትዮጵያ ክለብም ሆነ የውጪ ሁሉንም እናከብራለን፡፡ ሁሌም አጥቅተን እንዲሁም ጥሩ ለመጫወት እንሞክራለን፡፡ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንሞክራለን፡፡”
ስለተጎዱ ተጫዋቾች
“ (ተስፋዬ አለባቸው) በቡድኑ ውስጥ መካተቱትን ቅዳሜ የምናየው ይሆናል፡፡ ስለጉዳት የማውራት እምብዛም አልፈልግም፡፡ 21 ተጫዋቾች በልምምዱ ላይ ነበሩ፡፡ 18ቱ ውስጥ መግባት የሚችሉ በቂ ተጫዋቾች አሉን፡፡”
ስለ ደርቢው
“ጨዋታው ቀላል ይሆናል የሚል አስተያየት የለኝም፡፡ እንደምታውቁት ኢትዮጵያ ቡና ሰርቢያዊ አሰልጣኝ አለው፡፡ አውሮፓዊ የስራ ባልደረባዬ ነው፡፡ እንደማስበው ነገሮችን ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ሰው ነው፡፡ ቡድኑን ያደራጃል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ጨዋታው የተለየ ነው ፤ ልክ እንደ ፍፃሜ ጨዋታ፡፡ በሊቨርፑል ሊቨርፑል ከኤቨርተን እንዲሁም በማንቸስተር ማንቸስተር ዩናይትድ ከሲቲ ይጫወታሉ፡፡ ይህም ጨዋታ እንደዛው ነው፡፡ ከጨዋታው በፊት፣ መሃከል እና በኃላ አዲስ አበባ ሰላም ትሆናለች ብዬ አስባለው፡፡ የተሻለው ቡድን ያሸንፋል ብዬም አስባለው፡፡”