የጨዋታ ሪፖርት | “ወንድማማቾች ደርቢ” በሲዳማ ቡና የበላይነት ተጠናቋል

በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ይርጋለም ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

በአከባቢው አጠራር “ሩዱዋ” ወይም የወንድማማቾች ደርቢ እየተባለ የሚጠራው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተጠበቀውን ያህል ተመልካች ሳይታደምበት ቀርቷል፡፡

በኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ፊሽካ አብሳሪነት በተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳ ከተማዎች ከሲዳማ ቡና የተሻለ እንቅስቃሴን ቢያደርጉም በጠንካራ መከላለከል እና በመልሶ ማጥቃት የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር 9 ደቂቃ ብቻ ፈጅቶባቸዋል፡፡ አዲስ ግደይ ከመስመር በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ በረከት አዲሱ አስቆጥሮ ሲዳማን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀውም በባለሜዳዎች መሪነት ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡናዎች ዳግም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የሀዋሳ ከተማን ግብ ክልል ሲፈትሹ ተስተውሏል፡፡

በ51ኛው ደቂቃ መድሀኔ ታደሰ ለፍርድ አወቅ ሲሳይ አመቻችቶ አቀብሎት የባከነችው ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ ሀዋሳ ከተማን አቻ ለማድረግ እና የጨዋታውን መልክ ለመቀየር የተቃረበች ሙከራም ነበረች፡፡

ሲዳማ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቀጠር ጫና ፈጥረው በመጫወት በ61ኛው ደቂቃ ትርታዬ ደመቀ ያሻማውን የማዕዘን ምት ፍፁም ተፈሪ ወደ ግብን ቀይሮ የሲዳማን መሪነት ወደ  2 ከፍ አድርጓል፡፡ ለግቧ መቆጠር የሀዋሳ ተከላካዮች ስህተት አስተዋፅኦ ነበረው፡፡

ከዚች ግብ መቆጠር በኃላ ሀዋሳዎች ግብ በማስቆጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢምክሩም የሲዳማን ተከላካይ ሰብሮ መግባት አልቻሉም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተከላካዩ ፀጋዬ ባልቻ በ84ኛው ደቂቃ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አዲስ ግደይ የሲዳማን ግብ ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል፡፡

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ከደስታ ዮሀንስ የተቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ጃኮ አራፋት ቢያስቆጥርም ሀዋሳን ከሽንፈት መታደግ አልቻለም፡፡ ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ድሉን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 14 በማድረስ ወደ መሪዎቸ ጎራ ተቀላቅሏል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

በጨዋታው አዝኛለው፡፡ እንደጠበኩት አይደለም ያገኘሁት፡፡ እጅግ አዝኛለው በተደጋጋሚ ተሸንፈናል ቋሚ ተጫዋቾቼን በጉዳት እና በቅጣት አጥቻለው፡፡ ከተስፋ ባደጉት ነው የተጫወትኩት፡፡ በዛሬው ጨወታ ሲዳማዎች የተሻሉ ስለነበሩ ማሽነፍ ይገባቸዋል፡፡ በቀጣይ ስተታችንን ለማረም እንሰራለን። ”

አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

“በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል ፤ ያሰብኩትም ተሳክቶልኛል፡፡ በልጠን ተጫውተናል ፤ በጨዋታው የቡድኔን አቅም በሚገባ ተመልክቻለው፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎች ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት ለመምጣት እንሞክራለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *