የጨዋታ ሪፖርት፡ የዳዋ ሁቴሳ ብቸኛ ግብ አዳማን 3 ነጥብ አስጨብጣለች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ጅማ አባ ቡናን በኦሮሚያ ደርቢ ያስተናገደው አዳማ ከተማ በዳዋ ሆጤሳ ግብ 1-0 አሸንፎ ሙሉ ሶስት ነጥብ አሳክቷል፡፡

በ1908 የተቆረቆረችው አዳማ ከተማ የተመሰረተችበትን 100ኛ ዓመት እያከበረች ስለነበር ጨዋታው የተጀመረው 10፡00 ሰዓት ነበር፡፡ ከጨዋታው አስቀድሞም በሳለፍነው ሳምንት ህይወቱ ላለፈው ለጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የአንድ ደቂቃ ህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

በቁጥር የበዛ ተመልካች በተገኘበት ጨዋታ አዳማ ከተማዎች በጅማ አባ ቡና ላይ የጨዋታ እና የግብ ሙከራ የበላይነትን ይዘው ታይተዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ 10 ደቂቃዎች ውስጥ አዳማዎች በታፈሰ ተስፋዬ እና ጥላሁን ወልዴ ያልተሳኩ ሶስት የግብ ማግባት ሙከራዎን አድርገዋል፡፡

የጨዋታው የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራ በ14ኛው ደቂቃ ሚካኤል ጆርጅ ከግቡ ሁለት ሜትር ያገኘውን ኳስ በግቡ አናት ላይ የሰደዳት ነበረች፡፡ አባ ቡናዎች በ19ኛው ደቂቃ አሜ መሃመድ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የሞከረው ኳስ ሲሳይ ባንጫ አምክኖበታል፡፡ በአሜ ሙከራ የተነቃቁት አባ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ አዳማ የግብ ክልል መድረስ ከመቻላቸው ባሻገር ባለሜዳዎቹ ኳስን መስርቶ እንዳይጫወት በማድረግ ረገድ የተሳካ እንቅስቃሴን አሳይተዋል፡፡

በ28ኛው ደቂቃ ልደቱ ጌታቸው ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት የሞከረው ኳስ ሲሳይ አሁንም አምክኖታል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ባለሜዳዎቹ መሪ መሆን የሚችሉባቸውን ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች ሚካኤል ጆርጅ እና ዳዋ ሆቴሳ አምክነዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አዳማዎች ሙሉ ለሙሉ የማጥቃት ታክቲክን ሲከተሉ እንግዶቹ ወደ መከላከሉ ላይ አመዝነው ታይተዋል፡፡ በ47ኛው ደቂቃ ቡሩክ ቃልቦሬ ከግራ መስመር ጠርዝ የሞከረውን ሙከራ ጀማል ጣሰው ወደ ውጪ አውጥቶበታል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ሚካኤል በደረቱ አብርዶ ለሙጂብ ቃሲም ቢያመቻችለም የቀድሞ የሃዋሳ ከተማ ተጫዋች የመታው ኳስ በአባ ቡና ተከላካዮች ተጨርፎ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

በ58ኛው ደቂቃ ሚካኤል በግንባሩ የገጨውን ኳስ ጀማል ሲያድነው በቅርብ ርቀት የነበረው ሙጂብ ወደ ግብ ቢሞክርም ተከላካዬ በኃይሉ በለጠ በሚያስደንቅ ሁኔታ ኳስን ጨርፎ ወደ ውጪ አውጥቷል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኃላ አሁንም ሚካኤል ከ17 ሜትር በቮሊ የመታውን ኳስ ጀማል አውጥቶበታል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የነበረው ዳዋ የመታው ቅጣት ምት የግቡ አግዳሚን ለትሞ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ከደቂቃ በኃላ አዲስ ህንፃ ያሻገረለትን ኳስ ታፈሰ በግንባሩ ሞክሮ ጀማል በድንቅ ሁኔታ አድኖታል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሃያ ደቂቃዎች ሲቀሩ ጀማል የዳዋን ግሩም ቅጣት ምት አምክኖበታል፡፡ በ72ኛው ደቂቃ የአዳማው ግብ ጠባቂ ሲሳይ ከግብ ክልሉ ውጪ የአባ ቡና አጥቂ ሱራፌል አወል ላይ ጥፋት የሰራ ሲሆን በጥፋቱ በቀይ ካርድ ባለመውጣቱ የተከፉ የአባ ቡና ተቀያሪ ተጫዋቾች ብስጭታቸውን ገልፀዋል፡፡

በ76ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ የአዳማ ከተማን የመጀመሪያ እና ወሳኝ ግብ በቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ አባ ቡናዎች አጥቅቶ ለመጫወት ሲሞክሩ አዳማዎች ጨዋታው ለማቀዝቀዝ ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡

በጨዋታው መገባደጃ ላይ አዲስ በግንባሩ የገጨውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ ብቃት ላይ በነበረው ጀማል መክኖበታል፡፡

አዳማ ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን 18 በማድረስ ከደደቢት ጋር በዕኩል 17 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበልጦ የሊጉ አናት ላይ ይገኛል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሸናፊ በቀለ – አዳማ ከተማ

“ያው እንዳየኸው ጅማ ውጤቱን አጥብቦ ለመውጣት ነው የሄደው፡፡ ምንም ልታደረገው አትችልም፡፡ በቀጣይ ለማስተካከል እንሞክራለን፡፡ አብዛኛው ከአዳማ ጋር የሚጫወት ቡድን አቻን መሰረት አድረጎ ወይም ዘግቶ ስለሚጫወት ይህ ፈታኝ እየሆነብን ነው፡፡ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር መጫወቻ ቦታዎች እያሳጡን ነበር፡፡ ቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን፡፡”

“(ሲሳይ ቶሊ የተቀየረው) የሚፈለግበትን  ታክቲካል ዲሲፕሊን ስላሰራልኝ ነው፡፡ ሲሳይ በባለፉት ጨዋታዎች በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ተጫዋች ደግሞ ሁሌ ይጫወታል ማለት አይቻልም፡፡ በእርምት ቀጣይ ጥሩ ሆኖ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡”

“የተጋጣሚ ቡድን ዘግቶ ነው የሚመጣው፡፡ ለዚህም ነው አጥቂ የምናበዛው፡፡ ለመጫወት ቢፈልጉ ኖሮ ይህንን ያህል አጥቂ አናበዛም፡፡ ዛሬ አራት አጥቂ ነው የተጠቀምነው፡፡ ሁሉም ከአዳማ ጋር የሚጫወት ቡድን ዘግቶ ነው የሚመጣው፡፡ አሁን ላይ የተቸገርነው ነገር ይህ ነው፡፡”

“16ቱም ክለብ ዋንጫ አይበላም፡፡ እስከመጨረሻ የሄደ ቡድን ነው ቻምፒዮን የሚሆነው፡፡ ጠንክረን ከሄድን ዋንጫ እንወስዳለን ብዬ አስባለው፡፡ ጠንካራ ተወዳዳሪ መሆንም አንድ ሃብት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከሁለት ዓመት በፊት ነው ወደ ሊጉ ተመልሰን የመጣነው፡፡ አሁን ላይ እያሰመዘገበ የሚገኘው ውጤት ጥሩ ነው ብዬ አስባለው፡፡”

ደረጄ በላይ – ጅማ አባ ቡና

“ጨዋታው ምንም አይልም ፡፡ አዳማዎች በሜዳቸው ስለተጫወቱ የሜዳቸው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይዘነው የገባነው ታክቲክ ሁለት ነበር፡፡ አንዱ አቻ ለመውጣት እና እስከመጨረሻው ድረስ ድል ለማድረግ ነበር፡፡ ግን እነሱ የዳኛ ስጦታ ነበራቸው፡፡ የመጨረሻ ሰው የነበረው ግብ ጠባቂ ተጫዋች ጥሎ ዳኛው ምንም እርምጃ አልወሰደም ፤ ቢጫ ነው የሰጠው፡፡ በዳኛ ተበድለናል፡፡ ምክንያቱም ግብ ጠባቂው በቀይ ቢወጣ የራሳችንን ጥሩ ነገር መስራት እንችል ነበር፡፡ በዳኝነቱ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ሁለት ዕድል ይዘን ነበር የገባነው ያም ሆኖ ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ በቀጣይ ወደ አሸናፊነት እንመጣለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *