የ2015ቱ የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን በመወከል ሲሳተፍ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአልጄሪያው ኤም ሲ ኤል ኡልማ ጋር ባደረገው ጨዋታ በድምር ውጤት 2-2 ቢለያይም ከሜዳ ውጪ ባገባ በሚለው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ዛሬ በባህርዳር በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያስቆጠረው በኃይሉ አሠፋ ስለጨዋታው የሰጠው አስተያየት እንደሚከተለው ይቀርባል።
ስለ ጨዋታው
“በዛሬው ጨዋታ ከሁለት ጎል በላይ ማስቆጠር እንዳለብን ተረድተን ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ ማሊያ ያደረግኩት ሁለተኛ ጨዋታዬ ነበር። የመጀመሪያውንም ጎል እኔ ማስቆጠር ችያለሁ፤ በግቡም እንደማንኛውም ተጫዋች ደስ ብሎኛል። ነገር ግን ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር ባለማለፉ እጅግ አዝኛለሁ። በተለይ ከ500 ኪሎሜትር በላይ ተጉዞ ፀሃይ፣ ብርድ፣ ሰለቸኝ ሳይል ሊያበረታታን የመጣውን ደጋፊ በውጤት መካስ ባለመቻላችን ሁላችንም ከፍቶናል።
በእግርኳስ በምትፈጥራቸው ጥቂት ስህተቶች ብዙ ነገር ታጣለህ። ጥሩ መጫወት ብንችልም በሰራናቸው ጥቃቅን ስህተቶች ማለፍ ሳንችል ቀርተናል።”
ስለ ባህርዳር ስታዲየም
“የባህርዳር ስታዲየም በሃገራችን የተገነባ የመጀመሪያው ዘመናዊ ስታዲየም ነው። በአሁኑ ሰዓት በአዋሳ፤ በመቀሌ እና በሌሎችም ከተሞች ተመሳሳይ ስታዲየሞች በመገንባት ላይ ይገኛሉ። ኢንተርናሽናል ደረጃውን የጠበቀ ሜዳ በመሆኑ ሌሎችም ክልልሎች አርአያ መሆን ይችላል።”