ቅዱስ ጊዮርጊስ በአቡበከር ሳኒ ብቸኛ ጎል ወልድያን 1-0 በመርታት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።
10ኛው ሳምንት የኢትዮጽያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ በሊጉ ብዙ ግቦችን ያስቆጠረውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ጥቂት ግቦችን ካስተናገዱ ቡድኖች መካከል አንዱ ከሆነው ወልድያ ከተማ ጋር ያገናኘ ነበር። ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጀምሮ እየቀዘቀዘ በዘለቀው በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ወልድያዎች ከተጋጣሚያቸው እጅግ ተሽለው ታይተዋል።
የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታው ወልድያ በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ አብዛኛውን ሰዐት ከራሱ ጎል በተወሰነ መልኩ ራቅ ብሎ በሚከላከል እና በቅርብ ርቀት ከሚገኘው የአማካይ መስመሩ ጥሩ ሽፋን በሚሰጠው የተከላካይ ክፍሉ በመታገዝ የተጋጣሚውን ጥቃቶች በአግባቡ ሲመክት ታይቷል።
ቡድኑ በመከላከል ወቅት በመሀል ሜዳ ላይ ለጊዮርጊሶች ክፍተት ባለመስጠት እንዲሁም ኳስን ሲነጥቅ ከፊት ባሉት ሁለት አጥቂዎቹ አማካይነት ቶሎ ወደግብ ለመድረስ ጥረት በማድረግ ነበር የመጀመሪያውን አጋማሽ የጨረሰው። ወልድያዎች በዚህ የማጥቃት ሂደት በአንዷለም ንጉሴ ፣ በሀብታሙ ሸዋለም እና በሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ አማካይነት የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። የወልድያ የመጀመሪያ አጋማሽ መልሶ ማጥቃት በቂ ተጨዋቾችን በማጥቃት ወረዳው ላይ ቢያሳትፍ ምን አልባትም ግብ የሚያስቆጥርበትን ዕድል መፍጠር በቻለ ነበር።
ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው በኳስ ቁጥጥሩ በጥቂቱ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በ45+1ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ ከወልድያ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ካመከናት ኳስ ውጪ ያለቀላቸውን የግብ እድሎች በብዛት መፍጠር አልቻሉም። ከመስመር አጥቂዎቹ በቂ እገዛ ማግኘት ያልቻለው የቡድኑ የመሀል ክፍልም ይወሰድበት በነበረው የቁጥር ብልጫ ሳብያ የቡድኑን የማጥቃት አጨዋወት በአግባቡ ማገዝ ሳይችል ቀርቷል። ከተከላካይ ክፍሉ በቀጥታ ወደ አጥቂዎች ይላኩ የነበሩ ረጃጅም ኳሶችም በግዙፉ ግብ ጠባቂ ኤሚክሪል ቤሊንጌ እና በመሀል ተከላካዮቹ በቀላሉ ይመለሱ ነበር። በቂ እድል ያላገኙት ሶስቱ የፊት አጥቂዎች ዘካሪያስ ቱጂ ፣ አዳነ ግርማ እና አቡበከር ሳኒም የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ክፍል ማለፍ ተስኗቸው በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ለማየት ተችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በወልድያዎች ላይ ጫና ፈጥረው በመጫወት ከመጀመሪያው አጋማሽ በላይ ይበልጥ ወደግቡ የተጠጋውን የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ መስመር ለማስከፈት ሞክረዋል። ከአበባው ቡጣቆ በሚነሱ የቆሙ ኳሶችም የተወሰኑ እድሎችን ፈጥረው ነበር ። ቡድኑ ሳልሀዲን ሰይድ እና ራምኬል ሎክን ቀይሮ በማስገባት እና የፊት መስመሩን በማጠናከር ይበልጥ ተጭኖ ለመጫወት ያደረገው ጥረትም በ75ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቷል። ወልድያዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ጥሩ አጋጣሚ ወደግብ ምቀየር ተስኗቸው እና በፍጥነት ወደራሳቸው የግብ ክልል በመመለስ የመከላከል ቅርፃቸውን ከመያዛቸው በፊት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የፈጠሩትን እድል የቀኝ መስመር አጥቂው አቡበከር ሳኒ በአግባቡ በመጠቀም የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ወልድያዎች በመጠኑ ወደፊት በመጠጋት አቻ ለመሆን ጥረት አድርገዋል። በተለይም በ79ኛው ደቂቃ አንጋፋው አጥቂ አንዷለም ንጉሴ ተቀይሮ ከገባው ሌላው አጥቂ ጫላ ድሪባ በግንባር የተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ሞክሮ ፍሬው ጌትነት የያዘበት አጋጣሚ ቡድኑን ወደአቻነት ለመመለስ ትችል የነበረች ጥሩ አጋጣሚ ሆና አልፋለች። የወልዲያዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ከኋላ ክፍተቶችን የፈጠረላቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶችም የተለያዩ አጋጣሚዎች ጥቃት ቢሰንዝሩም ተጨማሪ ጎል ለምስቆጠር ግን አልቻሉም። በተለይ በ83ኛው ደቂቃ ላይ የወልድያ ተከላካዮችን 4 ለ 3 በሆነ የቁጥር ብልጫ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል መግቢያ አካባቢ ያገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪነታቸውን ለማስፋት የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ኳስ ባይበላሽባቸው ኖሮ ተጨማሪ አንድ ጎል ባስቆጠሩ ነበር። በዚህ ሁኔታ የቀጠለው ይህ ጨዋታም ሌላ ያለቀለት የግብ ሙከራ ሳይታይበት በአሰልጣኝ ማሪት ኖይ ቡድን የ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዚህ ውጤት መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ20 ነጥቦች ወደሁለተኛ ደረጃ ሲመጣ ወልድያ በበኩሉ በ10 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በ11ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሀዋሳ ሲያቀና ወልድያ በበኩሉ በአዲሱ የሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድየም የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን በማስተናገድ ይጀምራል፡፡