በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ባልተጠበቀ መልኩ ከሩብ ፍፃሜው በኤኳቶሪያል ጊኒ በአወዛጋቢ ሁኔታ ተሸንፈው የወደቁት የካርቴጅ ንስሮቹ በአዲስ አሰልጣኝ ለጋቦኑ ውድድር ቀርበዋል፡፡ ዋንጫ የማሸነፍ ግምት እምብዛም ባይሰጠቸውም በሃገር ውስጥ ሊግ በሚጫወቱ ተጫዋቾች የተዋቀረው ብሄራዊ ቡድን ብዙዎችን ሊያስደንቅ ይችላል፡፡
በ2004 ራሷ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ሞሮኮን አሸንፋ ዋንጫ ያነሳች ሲሆን ከ2004 ወዲህ ግን ቱኒዚያ እና አፍሪካ ዋንጫ ተገናኝተው አያውቁም፡፡ የካርቴጅ ንስሮቹ በተደጋጋሚ በአፍሪካ ዋንጫው መሳተፍ መቻላቸው እና ተስጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች መያዛቸው ቀላል ተጋጣሚ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት፡ 17
ውጤት፡ አንድ ግዜ አፍሪካ ቻምፒዮን (2004)
አሰልጣኝ፡ ሄንሪ ካስፐርዛክ
ቱኒዚያ በምድብ ሁለት ጎረቤቷ አልጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ከ10 ዓመት በኃላ ከተመለሰቸው ዚምባቡዌ ጋር ተደልድላለች፡፡ የ70 ዓመቱ የቱኒዚያ አሰልጣኝ ሄንሪ ካስፐርዛክ የፈረንሳይ እና ፖላንድ ጥምር ዜግነት አላቸው፡፡ ካሰፐርዛክ ጠንካራ የተከላካይ መስመር መገንባታቸው ዕምን ነው፡፡ ቡድኑ ላይ ግብ ማስቆጠር እጅግ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ካስፐርዛክ የቡድናቸውን ደካማ ጎኖች ከግብፅ እና ዩጋንዳ ጋር ባደረጓቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያዩ ሲሆን በፊት መስመር ላይ ያለው መሳሳትን በመቅረፍ ለውድድር መቅረብ አለባቸው፡፡ ቱኒዚያ የምድብ ተጋጣሚዎቿ ላይ ከቅርብ ግዜያት ወደዲህ የተሻለ የበላይነት መያዟ በስነልቦና ረገድ ጠቀሜታ አለው፡፡
ተስፋ
የቱኒዚያ ትልቁ ተስፋ ያላት ጠንካራ የተከላካይ ስፍራ ነው፡፡ የተከላካይ መስመሩ በአይመን አብደኑር የሚመራ ነው፡፡ የግራ መስመር ተከላካዩ አሊ ማሎል ከመከላካሉ ባሻገር ወደፊት በመሄድ ማጥቃት ላይ ጥሩ ነው፡፡ በግብ ጠባቂነት አይመን ማትሉቲ ይገኛል፡፡ ማትሉቲ ጥንካሬው ለክለቡ ኤቷል ደ ሳህል በ2016 በሚገባ አስመስክሯል፡፡ የነዚህ ጠንካራ የሆኑ ተጫዋቾች ስብጥርን የያዘው የተከላካይ ክፍሉ አስፈሪ መሆኑ ለሌሎች ቡድኖች ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም በመሃል ክፍሉ ዋሂብ ካዚሪ እና ፈርጃኒ ሳሲን የያዘ ሲሆን ጥበበኛው የሱፍ ሳክኒም ወደ ቀድሞ ብቃቱ እየተመለሰ ነው፡፡ ይህ ለቱኒዚያ ከምድቡ ለማለፍ ትልቅ ተስፋን እንድትሰንቅ ያደርጋታል፡፡ ከ2015 በአውዛጋቢ ሁኔታ ከውድድር ከወጡ በኃላ በአዕምሮ ረገድ ቡድኑ ጥንካሬን ማሳየቱ ሌላው ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡ ቡዙዎቹ ተጫዋቾች ከሃገር ውስጥ ሊግ መመረጣቸውም አሰልጣኙ ቡድናቸውን በቀላሉ ለማቀናጀት ይረዳቸዋል፡፡ ከ23ቱ የቱኒዚያ ተጫዋቾች 14ቱ የተመረጡት ከቱኒዚያ ሊግ 1 ከሚጫወቱ ክለቦች ነው፡፡
ስጋት
የተከላካይ መስመሩ ጠንካራ እንደሆነው ሁሉ የአጥቂ መስመሩ ግብ አስቆጣሪ እና የሚፈጠሩ የግብ እድሎችን መጨረስ የሚችል የፊት መስመር ተሰላፊ ይጎለዋል፡፡ በማጣሪያው ጨዋታ 16 ግቦችን ቱኒዚያ ብታስቆጥርም አብዛኞቹ ግቦቹ የተቆጠሩት የሰፋ የእግርኳስ ልዩነት ባላት ጅቡቲ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጃዚሪ፣ ኤሳም ጆምአ፣ ዶ ሳንቶስ እና ቺካዊን የመሳሰሉ አጥቂዎች ያፈራው ብሄራዊ ቡድን በጨራሽ አጥቂ ዕጥረት እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ በቻን 2016 እና በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ግቦችን ሲዋህድ የነበረው አጥቂው አህመድ አኪያቺ ከኤቷል ደ ሳህል ወደ ሳውዲው ታላቅ ክለብ ኢትሃድ ጅዳ ካመራ በኃላ ለካርቴጅ ንስሮቹ የሚሰጠው ግልጋሎት ቀንሷል፡፡ የአውሮፓ እግርኳስ ልምድ ያለው ሳብር ካሊፋ ከዚህ ቀደም የነበረው ብቃቱ አሁን ላይ የለም፡፡ የጠንካራ የተከላካይ ስፍራ መያዝ ጥሩ ጎን ሆኖ ሳለ ግብ የማያስቆጥር የአጥቂ መስመር ደግሞ ለቱኒዚያ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞ አስጊ ነው፡፡
የሚጠበቁ ተጫዋቾች
በካታር የሚጨዋተው የሱፍ ሳክኒ ሊመለከቱት የሚገባ ተጫዋች ነው፡፡ ሳክኒ ለአጥቂዎች ያለቀላቸውን ኳሶች ከማቀበሉም ባሻገር በሚያስቆጥራቸው ድንቅ ግቦች ተለይቶ ይታወቃል (በ2013 አፍሪካ ዋንጫ አልጄሪያ ላይ በመጨረሻው ደቂቃ ያስቆጠራት የማሸነፊያ ግብ በብዙዎች ዘንድ የተወደሰች ነበረች)፡፡ አል አሃሊን በዓመቱ መጀመሪያ የተቀላቀለው የግራ መስመር ተከላካዩ አሊ ማሎል አይናችንን ልንጥልበት የሚገባ ተጫዋች ነው፡፡ ማሎል የአፍሪካ እግርኳስን ለሚከታተሉ ሰዎች እንግዳ አይደለም በሴፋክሲያን ቆይታው የቱኒዚያ ሊግ 1 ኮከብ ግብ አግቢ ነበር (አብዛኞቹን ግቦች በፍፁም ቅጣት ምት ነው ያስቆጠረው)፡፡ ማሎል የቆመ ኳስ አጠቃቀሙም መልካም የሚባል ነው፡፡ የኤቷል ደ ሳህሉ አማካይ ሃምዛ ላምሃር በ2016 ክለቡ የቱኒዚያ ሊግ 1 እንዲያሸንፍ እንዲሁም የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ እንዲሆን አሰችሏል፡፡ ሃምዛ ደንቅ የቅጣት ምት መቺ ሲሆን የግብ ማስቆጠር ብቃቱ ቱኒዚያ ያለጥርጥር ይጠቅማታል፡፡ የመሃል ተከላካዩ አይመን አብደኑር እና አማካዩ ዋሂብ ካዝሪ ሌሎች ሊታዩ የሚገባቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
ቱኒዚያ በምድብ አንድ ከቶጎ፣ ጅቡቲ እና ላይቤሪያ ጋር ነበር የተደለደለችው፡፡ ጅቡቲ ላይ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር ማጣሪያውን የጀመረችው ቱኒዚያ ካደረገቻቸውን ስድስት ጨዋታዎች አራት አሸንፋ አንድ ተሸንፋ እንዲሁም አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርታ በ13 ነጥብ ምድቡን በመሪነት አጠናቅቃለች፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ራሚ ጀሪዲ (ሴፋክሲየን/ቱኒዚያ)፣ አይመን ማትሉቲ(ኤቷል ደ ሳህል/ቱኒዚያ)፣ ሞየዝ ቤንሸሪፋ (ኤስፔራንስ/ቱኒዚያ)
ተከላካዮች
ሳም ቤን የሱፍ (ኬን/ፈረንሳይ)፣ አይመን አብደኑር (ቫሌንሲያ/ስፔን)፣ ዘይድ ቦጋታስ (ኤቷል ደ ሳህል/ቱኒዚያ)፣ ስሌማን ቾክ (ሴኤቢ/ቱኒዚያ)፣ ሸምሰዲን ዳዎአዲ (ኤስፔራንስ/ቱኒዚያ)፣ አሊ ማሎል (አል አሃሊ/ ግብፅ)፣ መሃመድ ያኮቢ (ካይኩር ሪዚስፖር/ቱርክ)፣ ሃምዛ ማትሉቲ (ሴፋክሲየን/ቱኒዚያ)፣ ሃምዲ ናጉዝ (ኤቷል ደ ሳህል/ቱኒዚያ)
አማካዮች
ሃምዛ ላምሃር (ኤቷል ደ ሳህል/ቱኒዚያ)፣ ዋሂብ ካዝሪ (ሰንደርላንድ/እንግሊዝ)፣ ፈርጃኒ ሳሲ (ኤስፔራንስ/ቱኒዚያ)፣ መሃመድ ቤን አሞር (ኤቷል ደ ሳህል/ቱኒዚያ)፣ ፍራንሲስ አዞኒ (ኒምስ/ፈረንሳይ)፣ አህመድ ካሊል (ክለብ አፍሪካ/ቱኒዚያ)፣ ነይም ሲሊቲ (ሊል/ፈረንሳይ)
አጥቂዎች
ሳብር ካሊፋ (ክለብ አፍሪካ/ቱኒዚያ)፣ አህመድ አኪያቺ (ኢትሃድ ጅዳ/ሳውዲ አረቢያ)፣ የሱፍ ሳክኒ (ሉክዊያ/ካታር)፣ ጠሃ ያሲን ካኒሲ (ኤስፔራንስ/ቱኒዚያ)
ቱኒዚያ የምድብ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዕሁድ ሴኔጋልን በመግጠም ትጀምራለች፡፡