የጨዋታ ሪፓርት| ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሊጉ መሪ አዳማ ከተማን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን መርሃግብር ሊጉን በ21 ነጥብ በመምራት ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል፡፡

9፡00 እንዲጀመር ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የቅድመ ሆስፒታል የጤና አገልግሎት የሚሰጠው የጠብታ አንቡላስ እና የጤና ባለሙያዎቹ በወቅቱ በሜዳው ባለመገኘታቸው በጨዋታው ኮሚሽነር ትእዛዝ መሠረት በስፍራው እስኪደርሱ ድረስ ለ20 ደቂቃዎች ዘግይቶ ተጀምሯል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው ተሽለው በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ተሽለው ተገኝተዋል፡፡ በዚህም አዳማ በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች 3 ጥሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በተለይም በ6ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከላካዮች ስህተት ታግዞ ቡልቻ ሹራ አግኝቶ የሞከራትና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ እንዲሁም በ14ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮብ ፔንዜ በቀጥታ የመታውን ኳስ ቡልቻ ሹራ አግኝቶት ከግብ ጠባቂው አናት በላይ ለማስቆጠር ጥረት አድርጎ ኳሷ ከግቡ አናት በላይ ወጥታለች፡፡

በ19ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከአዳማው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ጥላሁን ወልዴ ነጥቆ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ፒተር ንዋድኬ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመምጣት የክለቡን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ አዳማ ከተማዎች በረጃጅሙ ከመሀል ተከላካዮች እንዲሁም ከግብ ጠባቂው በሚላኩ ኳሶች በመጠቀም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በዚህም በ36ኛው ደቂቃ ላይ በቀጥታ ከተከላካዮች የተላከለትን ኳስ ሚካኤል ጆርጅ በግንባሩ በመግጨት ያመከናት ኳስ ተጠቃሽ የግብ ሙከራ ነበረች፡፡

በ39ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንኮች ከቀኝ መስመር በአዲሱ ሰይፉ አማካይነት ያሻሙትን ኳስ ቢኒያም በላይ ቢያስቆጥርም የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነበር በማለታቸው ግቧ ሳትፀድቅ ቀርታለች፡፡

በ45ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ35ሜትር አካባቢ ፋሲካ አስፋው ያሻማውን ቅጣት ምት ቡልቻ ሹራ ሸርፏት የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ፌቮ ሲተፋው በድጋሚ ቡልቻ አግኝቶ ያመከናት በአዳማ ከተማዎች በኩል የመከነች የምታስቆጭ ግልጽ የማግባት አጋጣሚ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በንጽጽር ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተከላክለው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡

በ57ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ለባዶ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ ግቡን ተከትሎ ዋና ዳኛው እና ረዳት ዳኛው የተለያየ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተከትሎ ውዝግብ አስነስቷል፡፡ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾችም ግቧ ከጨዋታ ውጪ ነበረች በማለት ተቋውማቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡

ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኃላ አዳማ ከተማዎች በሙሉ ሀይላቸው ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል ነገር ግን ግልፅ የግብ እድሎችን መፍጠር አልቻሉም ፡፡ በ76ኛው ደቂቃ ቡልቻ ሹራ ሞክሮ ኢማኑኤል ፌቮ ያዳነበት እንዲሁም በተደጋጋሚ ዳዋ ሆቲሳ ከቋሙ ኳሶች በቀጥታ የሞከራቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች በተለይም አምበሉ ተስፋዬ በቀለ እንዲሁም ሌላኛው የመሀል ተከላካይ ሞኞት ደበበ ጨዋታውን የመሩት ዳኞች ላይ ተቃውማቸውን አሰምተዋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን ወደ 12 ከፍ በማድረግ በ10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ተሸናፊው አዳማ ከተማ አሁንም ተከታዮቹ በነገው እለት ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ አሁንም በ21ነጥብ ሊጉን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *