ዚምባቡዌ ከአስር ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ አህጉሪቱ ታላቅ ውድድር ብቅ ብላለች፡፡ እምብዛም የአፍሪካ ዋንጫ ልምድ የሌላት ዚምባቡዌ በእግርኳስ ከሚልቋት ሶስት ጠንካራ ሃገራት ጋር መመደቧ ዝቅተኛ ግምትን እንዲሰጣት አድርጓል፡፡
ጦረኞቹ የሚመሩት በራሳቸው ሃገር ዜጋ በሆነ አሰልጣኝ ሲሆን ብዙዎቹ ተጫዋቾቻቸው ከደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ሊጎች የመጡ ናቸው፡፡ ብዙዎች ዚምባቡዌ ከዚህ ምድብ ለማለፍ ተዓምር ያስፈልጋታል ይላሉ፡፡ ከጫና ነፃ የሆነው ብሄራዊ ቡድን ማንም ያልጠበቀውን ውጤት ሊያስመዘግብም ይችላል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 2
ውጤት፡ የምድብ ተፋላሚ (2004 እና 2006)
አሰልጣኝ፡ ካሊስቶ ፓስዋ
ዚምባቡዌ ከ2006 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ በምትሳተፍበት የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሁለት ከአልጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ቱኒዚያ ጋር ተደልድለዋል፡፡ የ46 አመቱ አሰልጣኝ ፓሰዋ ካሊስተስ የዚምባቡዌ ሊግ ተወዳዳሪ የሆነውን ዳይናሞስ ያሰለጠኑ ሲሆን ሃገራቸውን ከአመታት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በመመለስ የተሻለ ስራ ሰርተዋል፡፡ የዚምባቡዌ ተጫዋቾች በጨዋታ ቦነስ ተገቢነት ዙሪያ ባቀረቡት ጥያቄ ከዚፋ (ዚምባቡዌ እግርኳስ ፌድሬሽን) ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ይህ አለመግባባት ቢፈታም ከአፍሪካ ዋንጫ መጀመር ቀናት በፊት በመፈጠሩ የቡድኑን ስሜት እንዳያበላሸው ይሰጋል፡፡ የቢቢሲ ስፖርት ዚምባቡያዊው ጋዜጠኛ ፋራይ ሙጋንዚ ጦረኞቹ ለፍፃሜ የሚደርሱ ከሆነ በውስጥ ሱሪ ብቻ ወደ ስታደ አሚቲ ለመምጣት ቃል ገብቷል፡፡ ዚምባቡዌ እውነትም ከምድብ ካለፈች ትልቅ ውጤት ይሆናል፡፡
ተስፋ
ዚምባቡዌ ከጫና ነፃ ሆኗ ለውድድር መግቧቷ አንዱ ሊጠቅማት የሚችል ነገር ነው፡፡ በዚምባቡዌ እና ምድቡ ውስጥ ባሉ ሶስት ሃገራት መካከል ያለው የሰፋ ልዩነት ጫናው ከዚምባቡዌ ይልቅ ወደ ሌሎቹ ሃገራት እንዲያመራ አድርጓል፡፡ ቡድኑ በአብዛኛው በወጣቶች የተዋቀረ መሆኑ ሌላኛው ጠንካራ ጎን ነው፡፡
ጦረኞቹ የያዟቸው የፊት መስመር ተሰላፊዎች እድሎችን ካገኙ የጨዋታ ውጤት የመለወጥ ብቃት አላቸው፡፡ የአጥቂ አማካዩ ካማ ቢሊያት ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ለቡድን አጋሮቹ የመቀባበያ አማራጮችን በመፍጠር ቡድኑ ሲያጠቃ እንዳይቸገር ይረዳል፡፡ ቡድኑ ጥሩ እግርኳስን ከመጫወቱ ባሻገር በመስመር ላይ ጥሩ የሆኑ ተጫዋቾች አሉት፡፡ ቡድኑ እርስ በእርስ የሚግባቡ ተጫዋቾችን መያዙ እና የተሰጣቸው ቀላል ግምት በአፍሪካ ዋንጫ ጉዞቸው ላይ ሊጠቅማቸው ይችላል፡፡
ስጋት
የአፍሪካ ዋንጫ ልምድ የሌላት ዚምባቡዌ ከምድብ ሁለት በየትኛው መንገድ እንደምታልፍ አጠያያቂ ነው፡፡ የቡድኑ አብዛኞቹ ተሰላፊዎች ለአፍሪካ ዋንጫው ይሁን ለትልቅ ውድድር አዲስ ናቸው፡፡ ይህ ልምድ ማጣት የዚምባቡዌ ጉዞ ላይ እክል እንዳይፈጥር ያሰጋል፡፡ በአጨራረስ ብቃታቸው የማይታሙ አጥቂዎችን ብትይዝም ለአጥቂዎች ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን አመቻችቶ የሚያቀብል ፈጣሪ አማካይ በቡድኑ ውስጥ አለመታየቱ የአሰልጣኝ ካሊስተስ ጭንቀት ነው፡፡
ሊታዩ የሚገባቸው ተጫዋቾች
ዚምባቡዌ አሁን ላይ በአፍሪካ ከሚጫወቱ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል ከሚሰለፈው ካማ ቢሊያት ላይ መተማመን ትችላለች፡፡ ቢሊያት ክለቡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ እንዲሆን ከፍተኛ ሚናን የተጫወተ ሲሆን ወሳኝ ግቦቹ ሃገሩን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ወስዷል፡፡ ፈጣኑ የአጥቂ አማካይ ቢሊያት ጦረኞቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ጉዞአቸው መሳካት የሚፈልጉት ተጫዋች ነው፡፡ በካይዘር ቺፍ ቆይታ የነበረው ኖሌጅ ሙሶና ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ ያገኛቸውን አጋጣሚዎች በመጨረስ የተዋጣለት የሆነው ሙሶና በቂ ልምድ ያለው መሆኑ ዚምባቡዌን እጅጉን ይጠቅማል፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
ዚምባቡዌ በምድብ 12 ከስዋዚላንድ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር ተደልድላ ነበር፡፡ ካለፉት ሃገራት መካከል ዚምባቡዌ በነጥብ የተሻለችው ከጊኒ ቢሳው ብቻ ነው፡፡ ዚምባቡዌ ካደረጋቻቸው 6 ጨዋታዎች በሶስቱ ስታሸንፍ በአንድ ነጥብ ተጋርታ ኮናክሬ ላይ በጊኒ 1-0 ተሸንፋለች፡፡ ዚምባቡዌ ምድቡን በ11 ነጥብ በመሪነት ስታጠናቅቅ ያስቆጠረችው ግብ 11 ሲሆን 4 ግቦችን በአንፀሩ አስተናግዳለች፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ዶኖቫን በርናርድ (ሃውማይን/ዚምባቡዌ)፣ ታካባቫ ማዋያ (ዚፒሲ ካሬባ/ዚምባቡዌ)፣ ታቴንዳ ሙኩሩቫ (ዳይናሞስ/ዚምባቡዌ)
ተከላካዮች
ኮስታ ናሞኒሱ (ስፓርታ ፕራግ/ቼክ ሪፐብሊክ)፣ ሃርድላይፍ ቪሪኪዊ (ካፕስ ዩናይትድ/ዚምባቡዌ)፣ ኤሊሳ ሞሮዋ (ንጊዚ ፕላቲኒየም ስታርስ/ዚምባቡዌ)፣ ኦኒስሞር ባሴራ (ሱፐርስፖርት ዩናይትድ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ቲኔጅ ሃድቤ (ቺክን ኢን/ዚምባቡዌ)፣ ላውረንስ ማላንጋ (ቺክን ኢን/ዚምባቡዌ)፣ ኦስካር ማቻፓ (ኤኤስ ቪታ/ዲ.ሪ. ኮንጎ)
አማካዮች
ዳኒ ፒሪ (ጎልደን አሮስ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ኢቫንስ ሩሳይክ (ማርቲዝበርግ ዩናይትድ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ኩዳኩዋዴ ማሃቺ (ጎልደን አሮስ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ብሩስ ካንጋዋ (አዛም/ታንዛኒያ)፣ ዊላርድ ካትሳንዴ (ካይዘር ቼፍ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ማርቭለስ ናካምባ (ቪትስ አርነም/ቤልጂየም)፣ ካማ ቢሊያት (ማሜሎዲ ሰንዳውንስ/ደቡብ አፍሪካ)
አጥቂዎች
ኖውሌጅ ሙሶና (ኦስተንድ/ቤልጂየም)፣ ታይሬል ማቲዩ ሩሳይክ (ሄልሰንቦርግ/ስዊድን)፣ ሊበርቲ ሙሽክዊ (ዳሊያን ዩፋንግ/ቻይና)፣ ፓሽን ንዶሮ (ኦርላንዶ ፓይሬትስ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ኩትበርት ማላጂላ (ቢድቬስት ዊትስ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ፊላና ካድዌር (ጁርጋርደንስ/ስዊድን)
ዚምባቡዌ የምድቡ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዋን አልጄሪያን ፍራንስቪል ላይ ዕሁድ በመግጠም ትጀምራለች፡፡