ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና ፡ ቻምፒዮኑን ፍንጭ የሚሰጥ ፍልሚያ

ከግምት ውጪ የሆኑ ውጤቶች እየተመዘገቡበት የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወደ ወሳኝ ምእራፍ ተሸጋግሯል፡፡ በ18ኛው ሳምንት ቅዳሜ 10:00 ላይ የሚደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ፍልሚያም ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝት ያለው ጨዋታ ነው፡፡

በ35 ነጥቦች ሊጉን እየመራ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ባለፈው ሳምንት አርባምንጭ ከነማን 2-0 አሸንፎ ለሰአታት የተነጠቀው መሪነትን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክቧል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከመከላከያ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአቻ ውጤት ፈፅሞ ከሲዳማ ቡና በ3 ነጥቦች ለመራቅ ተገዷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና በሁለተኛው ዙር

ሁለቱ ክለቦች በሁለተኛው ዙር ሊጉን እየተፈራረቁ መምራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና የሜዳው ሁለት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ከሜዳው ውጪ ያደረጋቸውን በአቻ ውጠት ፈፅሞ ምንም ሽንፈት አላስተናገደም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ አዲስ አበባ ላይ ሁለት አሸንፎ አንድ አቻ ሲለያይ ሀዋሳ ላይ ሽንፈት አስተናግዶ ተመልሷል፡፡

የተለመዱ ፊቶች

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊግ ዋንጫ ያነሱት አንዱአለም ንጉሴ ፣ ኤሪክ ሙራንዳ ፣ ፍፁም ተፈሪ እና ሞገስ ታደሰ ለሌላ የሊግ ድል ከሲዳማ ቡና ጋር ጥሩ ጉዞ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከሲዳማ ቡና ጋር ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ቢያድግልኝ ኤልያስ ደግሞ ሲዳማ መንገድ ላይ ቆሟል፡፡

 

ቁልፍ ፍጥጫዎች

ኤሪክ ሙራንዳ ከ ሮበርት ኦዶንግካራ

ኬንያዊው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ አሁን በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረ ሲሆን በተከታታይ ሁለት ጨዋዎች ሲረበሽ የነበረውን የጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ይፈትናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ በተከታታይ ጨዋታዎች ቅዱ ጊዮርጊስ ነጥቦች ይዞ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ በተለይም ከድቻ እና መከላከያ ጋር በነበሩ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ይዞ የወጣው በዩጋንዳዊው ብርታት ነበር፡፡ በዚህም ጨዋታ ፈረሰኞቹን ከቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጣማሪዎች ጥቃት ይመክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በኃይሉ አሰፋ ከ አብዱልከሪም መሃመድ

ሁለቱም በድንቅ አቋም ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ሁለቱን የሚያፋጥጠው መስመርም የጨዋታው ወሳኝ ክፍል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የቅዱ ጊዮርጊስ የግብ እድሎች የሚመነጩት ከበኃይሉ አሰፋ ሲሆን የሲዳማ ቡና ጠንካራ መስመርም በአብዱልከሪም እና እንዳለ ከበደ የሚመራው ግራ መስመር ነው፡፡

አዳነ ግርማ ከ ሞገስ ታደሰ

አዳነ አቋኑ ወርዷል በሚል ከብዙዎች ወቀሳ ቢቀርብበትም አሁንም የቅዱስ ጊዮርጊስን የፊት መስመር የሚመራው ግዙፉ አጥቂ ነው፡፡ ዘንድሮ በመሃል ተከላካይነት እየተጫወተ የሚገኘው ሞገስ ከአዳነ የሚያደርጉት ፍልሚያም የጨዋታውን ውጤት የመወሰን አቅም አለው፡፡

10682388_385170924984983_6800229039321923495_o

እውነታዎች

-ሲዳማ ቡና ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አላስተናገደም፡፡ ከንግድ ባንክ እና ኤሌክትሪክ አቻ ሲለያይ ደደቢት እና መከላከያን አሸንፏል፡፡

-ቅዱስ ጊዮርጊስ በሲዳማ ቡና ሽንፈት አስተናግዶ አያውቅም፡፡

-ቅዱስ ጊዮርጊስ አምና የሊጉ ቻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው ሲዳማ ቡናን 1-0 ባሸነፈበት 21ኛ ሳምንት ነበር፡፡

-በመጀመርያ ዙር ባደረጉት ጨዋ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለሜዳው ሲዳማ ቡናን 2-0 አሸንፏል፡፡

-ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ጋር ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ውስጥ በ9 ጨዋታዎች ላይ ግብ አልተቆጠረበትም፡፡

-ሲዳማ ቡና አዲስ አበባ ላይ ሽንፈት ካስተናገደ አንድ አመት ሊሞላው ተቃርቧል፡፡ የይርጋለሙ ክለብ ለመጨረሻ ጊዜ ሽንፈት ያስተናገደው ግንቦት 13 ቀን 2006 ዓ/ም በኤሌክትሪክ 1-0 የተረታበት ነው፡፡

 

የእርስ በእርስ ግንኙነቶች

ተጫወቱ – 11

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸነፈ – 7

አቻ – 4

ሲዳማ ቡና አሸነፈ – 0

ቅዱስ ጊዮርጊስ አስቆጠረ – 16

ሲዳማ ቡና አስቆጠረ – 4

 

ያለፉት 5 ጨዋታዎች ውጤት

ቅዱስ ጊዮርጊስ – አቻ – ድል – ሽንፈት – ድል – አቻ (ደረጃ 2ኛ)

ሲዳማ ቡና – ድል – አቻ – ድል – አቻ – ድል (ደረጃ 1ኛ)

11074439_782044145218307_2767723310304015374_n

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *