የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ናይጄርያዊ አጥቂ ፊሊፕ ዳውዚ ትላንት ከአርባምንጭ ጋር 2-2 በተለያዩበት ጨዋታ ሁለቱንም የባንክ ግቦች በማስቆጠር የግብ ድምሩን 13 በማድረስ ከቢንያም አሰፋ ጋር የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደረጃ ተጋርቷል፡፡
ፊሊፕ ከጨዋታው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ስለ ቻምፒዮንነት ፉክክሩ እና የግል ክብር አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
‹‹ የትላንቱ ጨዋታ አስቸጋሪ ነበር፡፡ 5 ጨዋታዎች በተከታታይ አሸንፈን በመምጣታችን ጫናው የነበረው እኛ ላይ ነበር፡፡ ዛሬ ነጥብ ብንጥልም በተከታታይ ያስመዘገብናቸው ውጤቶች መልካም ናቸው፡፡ ከላያችን ያሉት ባለመራቃቸው አሁንም የዋንጫው ተፎካካሪ ነን፡፡ ››
ኬንያዊው ፍራንሲስ ቺንጂሊ በ1995 ለከፍተኛ ግብ አግቢነት ክብር ከተጠጋ ወዲህ ለሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት ክብር አትዮጵያውያን አጥቂዎችን የሚቀናቀን አጥቂ እምብዛም ሳይታይ ቆይቷል፡፡ ባለፉት 6 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ፊሊፕ ግን የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን የመጀመርያው የውጭ ዜጋ ለመሆን አልሟል፡፡
‹‹ የግብ አግቢነቱን ክብር ባገኝ ደስተኛ ነኝ፡፡ እስከሁን ማንም የውጭ ዜጋ ያላሳካውን ማሳካት ትልቅ ነገር ነው፡፡ የበድኔ አባላትም ግቦች እንዳስቆጥርና ክብሩን እንዳገኝ ያበረታቱኛል፡፡ ግብ ማስቆጠር ብወድም ለጓደኞቼ የግብ እድሎችም ማመቻቸት ያስደስተኛል፡፡ ያም ሆኖ የግብ አግቢነቱን ክብር በማሳካት ታሪክ መስራት እፈልጋለሁ፡፡ ›› ሲል አስተያየቱን ቃጭቷል፡፡