ፕሪሚየር ሊግ ፡ አዳማ ከነማ መከላከያን አሸነፈ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ ስታድየም ያቀናው አዳማ ከነማ መከላከያን 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሏል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት ባለፈው ሳምንት በመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈው ተክለወልድ ፍቃሱን ለማሰብ የመከላከያ ተጫዋቾች እና ኣባላት የተጫዋቹ ምስል እና ቁጥር ያለበት ቲሸርት ለብሰው እንዲሁም ባነር ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

አዳማ ከነማዎች ጨዋው በተጀመረ ገና በ56ኛው ሴኮንድ አምሃ በለጠ ባስቆጠረው ግብ 1-0 መምራት የጀመሩ ሲሆን በ14ኛው ደቂቃ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ዮናታን ከበደ እንግዳዎቹ 2-0 እንዲመሩ የምታስችለዋን ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን ግብ ለማስቆጠር ግን እስከ 83ኛው ደቂቃ ጠብቀዋል፡፡ ተቀይሮ የገባው ኡጉታ ኦዶክ ግብ አስቆጥሮ መከላከያዎች በመጨረሻ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው እንዲጫወቱ አድርጓቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በአዳማ ከነማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ የመከላከያው አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ውጤቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ ጨዋታው ባልጠበቅነው ሁኔታ ነው የተጀመረው፡፡ በትኩረት ማነስ ምክንያት ግቦች ተቆጥረውብናል፡፡ ተጫዋቻችንን ባጣንበት ማግስት መሸነፋችን አስከፍቶናል፡፡ ባይሳካም አሸንፈን ማስታወሻነቱን ለተክለወልድ ለመስጠት አስበን ነበር፡፡ ከስነልቦና አለመረጋጋት ለማገገም ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ ›› ብለዋል፡፡

የአዳማ ከነማ አቻቸው በበኩላቸው የቡድናቸው ህብረት ውጤት እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ ከሊጉ ጠንካራ ቡድኖች አንዱን በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ፡፡ የአዳማ ከነማ የቅርብ ጊዜ አቋም ጥሩ እንዲሆን ያደረገው ህብረታችን ነው፡፡ ስናጠቃ እና ስንከላከል ከተጋጣሚያችን የቁጥር ብልጫ እንወስዳለን፡፡ ታክቲካል ዲሲፕሊን ላይም ጥሩ ነበርን፡፡ ግቦች ካስቆጠርን በኋላ አፈግፍገን በመከላከል የምንፈልገውን አሳክተናል›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *