‹‹ አሰልጣኙ የሚሰጠኝን መመርያ ተግባራዊ ማድረጌ ውጤታማ አድርጎኛል ›› ዮናታን ከበደ

አዳማ ከነማ ዛሬ መከላከያን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ 2-1 በመርታት ደረጃውን ወደ 5ኛ አሻሽሏል፡፡ ከሁለቱ ግቦች አንዷን ከመረብ ያሳረፈው ዮናታን ከበደም ከጨዋታው በኋላ ስለ ጨዋታው እና ወቅታዊ ኣቋሙ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
አምና ኤሌክትሪክን ለቆ ዳሽን ቢራን የተቀላቀለው ዮናታን ከበደ እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ከ18 ወራት የክለቡ ቆይታ በኋላ አዳማ ከነማን ተቀላቅሏል፡፡ ዮናታን በዳሽን ስኬታማ ጊዜ እንዳያሳልፍ ያደረገው የሚሰጠው የጨዋታ እድል ዝቅተኛ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራል፡፡
‹‹ ዘንድሮ በመጀመርያው ዙር በዳሽን ተጠባባቂ ወንበር አሳልፌያለሁ፡፡ ምናልባት ለአሰልጣኙ አጨዋወት ተስማሚ ሳልሆን ቀርቼ ይሆናል፡፡ አምና ግቦችን በማስቆጠር ክለቡን ከመውረድ ባተርፍም ዘንድሮ አሰልጣኙ የሚፈልጋቸው ተጫዋቾችን በማምጣቱ ቋሚ ተሰላፊ ሆኜ ጨዋታዎችን መጀመር አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ በግማሽ ሲዝን እረፍት ላይ ከአሰልጣኙ ጋር በመነጋገር ዳሽንን ለቅቄ አዳማን ተቀላቅያለሁ፡፡ ››
የቀድሞው የሀዋሳ ከነማና እና ኤሌክትሪክ አጥቂ አሁን በአዳማ የተደላደለ ይመስላል፡፡ በ6 ጨዋታዎች 3 ግቦች ማስቆጠርም ችሏል፡፡ ዮናታን ስኬቱ ከአሰልጣኙ እና ክለቡ እንደመጣ ያብራራል ‹‹ በግል አሰልጣኙ የሚሰጠኝን መመርያ ተግባራዊ ማድረጌ ውጤታማ አድርጎኛል፡፡ እንደ ቡድን ደግሞ ክለቡ የተሸለ ደረጃ ላይ ሆኖ ካጠናቀቀ ከፍተኛ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚሰጠን ካል ስለተገባልን በከፍተኛ መነሳሳት እየተጫወትን እንገኛለን፡፡ ››
ዮናታን በአብዛኛው የፕሪሚየር ሊግ ተመልካች ተለይቶ የሚታወቀው ግብ ካስቆጠረ በኋላ ‹‹ ጌታ እኮ ነው ›› የምትል መንፈሳዊ መልእክት በማሳየት ነበር፡፡ አሁን አሁን ይህንን ማድረግ የተወው ዮናታን ምክንያቱን ይናገራል፡፡ ‹‹ ዳኞች ይህን ማድረግ እንደማይቻል በመግለፃቸው ግቦች ሳስቆጥር መልእክሩን ማሳየት አቁሜያለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የዛሬውን ግብ ባለፈው ሳምንት ሁለት የቤተሰብ አባላቸውን ላጡት የተክለወልድ ቤተሰቦች ማስታወሻነት አበርክቻለሁ፡፡ ›› ሲል ሃሳቡን አጠቃሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *