መሃመድ አህመድ – ከ ወልድያ
9፡05 ላይ የተጀመረው ጨዋታ በወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ሞቅ ብሎ ለሜዳውም የተለየ ድምቀት ሆኖ ውሏል፡፡
ጨዋታው በተጀመረ ገና በ3ኛው ደቂቃ ድቻዎች አደገኛ የግብ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን በእለቱ ዋናውን ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫን ተክቶ የገባው ቢንያም ተፈራ በአስደናቂ ሁኔታ አድኖታል፡፡
ወልድያዎች ከጨዋታው መጀመር አንስቶ አፈግፍገው መጫወትን የመረጡ ሲሆን በ10ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ አጥቂው ፍፁም ደስይበለው በግንባሩ በመግጨጽ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎ ወልድያን መሪ አድርጓል፡፡
ግቧ የወልድያ ደጋፊዎችን ዝምታ ስትሰብር ድቻዎች ደግሞ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው ለመጫወት ትረት አድርገዋል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ላይም ድቻዎች ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ቢሆንም ቢንያም ከግብ ክልሉ በመውጣት አድኗታል፡፡
በ37ኛው ደቂ ድቻዎች ሌላ የግብ አጋጣሚ የፈጠሩ ሲሆን አሁንም የግብ ጠባቂው ብርታት ወልድያ ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣ አድርጓል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ ልክ እንደ 1ኛው አጋማሽ ሁሉ የወላይታ ድቻ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የታየበት ቢሆንም በወልድያ ጠንካራ የመከላከል አጨዋወት ምክንያት እምብዛም የግብ ሙከራዎች አልታዩበትም፡፡
በ63ኛው ደቂቃ ቶክ ጀምስ ከሳሙኤል ደግፌ የተሸገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት በ66ኛው ደቂ ላይ ድቻዎች ፍፀም ያለቀለት የግብ እድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በእለቱ ድንቅ አቋሙን ያሳየው ቢንያም ኳሷን በአስደናቂ ቅልጥፍና ከመስመር ያወጣበት መንገድም ከደጋፊው አድናቆት ተችሮታል፡፡
በ69ኛው ደቂቃ አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ አጥቂቀው ፍፁም ደስይበለውን በተከለካይ አማካዩ ዳንኤል ዝናቡ ኋላ ላይ ደግሞ ማይክ ሰርጂን በሙሉቀን አከለ በመቀየር ውቴታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት የሞከሩ ሲሆን ድቻዎች በ5 ደቂዎች ውስጥ ሁለት የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የበለጠ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡
ጨዋታው በድቻ የግብ ሙከራ እና የኳስ ቁጥጥር በላይነት ቢቀጥልም የወልድያን የተከላካይ መስመር ማስከፈትና በእለቱ ከ4 በላይ ያለቀላቸው የግብ እድሎችን ያመከነው ቢንያም ተፈራ መረብ ላይ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በወልድያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡