በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የመክፈቻ ቀን መከላከያ እና ጅማ አባጅፋር ድል ቀንቷቸዋል

15ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ዛሬ በደማቅ ሁኔታ ሲጀምር በምድብ አንድ የተደለደሉት መከላከያ እና ጅማ አባጅፋር ተጋጣሚዎቻቸው የነበሩትን አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ውጤት አሸንፈዋል።

አዲስ አበባ ከተማ 0-2 መከላከያ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራን ጨምሮ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አስራት ኃይሌ (አሠልጣኝ) እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የተገኙበት የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት በማርሽ እና የሙዚቃ ባንድ በታጀቡ ጡዑመ ዜማዎች ታጅቦ ከተከናወነ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር መክፈቻውን አድርጓል። የዕለቱ የክብር እንግዶችም የአዲስ አበባ እና መከላከያ ተጫዋቾችን ሠላምታ ከሰጡ በኋላ 8:20 ላይ ጨዋታው ጀምሯል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት መከላከያዎች በተሻለ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ መጫወት ይዘዋል። በአስረኛው ደቂቃም ቡድኑ በሰመረ ሀፍቱ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ድንቅ ሙከራ በማድረግ መሪ ለመሆን ጥሯል። ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የመረጡት አዲስ አበባዎች በበኩላቸው ዘለግ ያለ ደቂቃ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው 24ኛው ደቂቃ ደርሷል።

በ24ኛው ደቂቃም የመከላከያ አዲሱ ፈራሚ ቢኒያም በላይ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ መረብ ላይ በማዋሀድ ጦሩ መሪ ሆኗል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር የያዙት የአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ተጫዋቾች ግብ ካስተናገዱ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ አቻ ለመሆን ጥረዋል። በዚህም ቡድኑ በግራ መስመር ወደ መከላከያ የግብ ክልል በማምራት በፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ ነበር። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ መከላከያ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው አቤል ነጋሽ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ዋኬኒ አዱኛ በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖታል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ተሻሽለው ወደ ሜዳ የገቡት የሚመስሉት አዲስ አበባ ከተማዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በ55ኛው ደቂቃ ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ቻርለስ ሪባኑ በግንባሩ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ለጥቂት መረብ ላይ ሳያርፍ ወጥቶበታል። ይህ ሙከራ ከታየ ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከጨዋታው ድል ለማግኘት የሚያስተማምናቸውን ጎል በእጃቸው ለማስገባት ወደ አዲስ አበባዎች የግብ ክልል ያመሩት መከላከያዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል።

በዚህም አዲሱ አቱላ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ለቡድኑ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምትም ቢኒያም በላይ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። በቀሪቹ ደቂቃዎች ሁለቱ ቡድኖች ሌላ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በመከላከያ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ቢኒያም በላይ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እጅ የዋንጫ እና 12 ሺ ብር ገንዘብ ሽልማቱን ተረክቧል።

ጅማ አባጅፋር 2-0 ኢትዮጵያ ቡና

ተጠባቂው የዕለቱ መርሐ-ግብር የሆነውን የኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባጅፋር ጨዋታን ለመታደም ደግሞ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊትም የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አስራት ኃይሌ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። በተለይ አቶ ኢሳይያስ ከረጅም ጊዜ በኋላ ደጋፊዎች ጨዋታዎችን ለማየት ስታዲየም በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በየሰከንዱ የኮቪድ ነገር እንደይረሳ አሳስበዋል። ይህ ጨዋታም እንደ መጀመሪያው መርሐ-ግብር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር ተጀምሯል።

ወደ ጎል በመድረሱ ረገድ ሻል ብለው የታዩት ጅማዎች ገና በጅማሮው ኳስ እና መረብን አገናኝተው መሪ ሆነዋል። በዚህም በ7ኛው ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ በውጪ እግሩ ወደ ጎል የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ እና የግቡ አግዳሚ ሲመልሱት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አዲሱ የቡድኑ ፈራሚ መሐመድኑር ናስር ግብ አድርጎታል። በጊዜ ግብ የተቆጠረባቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በ21ኛው ደቂቃ ሮቤል ኪሮስ ከርቀት በሞከረው ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል።

ኳሱን በሚገባ የተቆጣጠሩት ቡናዎች በ32ኛው ደቂቃ በአላዛር ሽመልስ አማካኝነት ሌላ ኳስ ከወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ሞክረው መክኖባቸዋል። ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸውን በመጠቀም የቡና ተከላካዮች ላይ ፈተና መስጠት የቀጠሉት አባጅፋሮች ደግሞ በ44ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ ላይ በተሰራ ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የተገኘውን አጋጣሚም ዳዊት ፍቃዱ ወደ ግብነት ቀይሮታል። አጋማሹም በጅማ አባጅፋር 2-0 መሪነት ተገባዶ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት የአሠልጣኝ ካሣዬ ተጫዋቾች ከጨዋታው ውጤት ይዞ ለመውጣት በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረዋል። አጋማሹ በተጀመረ በአምስተኛው ደቂቃም አላዛር በጥሩ የኳስ ቅብብል የደረሰውን የመጨረሻ ኳስ ከርቀት ሊያስቆጥረው ነበር። በተቃራኒው በመጀመሪያው አጋማሽ ሲከተሉት የነበረውን ፈጣን የማጣቃት እንቅስቃሴ ጋብ ያደረጉት ጅማዎች በ59ኛው ደቂቃ ከመዓዘን የተሻገረን ኳስ በመጠቀም መሪነታቸውን ወደ ሦስት ከፍ ለማድረግ ጥረው የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቡናዎች ከቅጣት ምት የተነሳን ኳስ በያብቃል ፈረጃ አማካኝነት ከመረብ ጋር ሊያዋህዱት ነበር።

አሁንም ጫና አሳድረው መጫወት የቀጠሉት ቡናዎች በ64ኛው ደቂቃ በተደራጀ መልኩ ወደ ጅማ የግብ ክልል ሄደው ግብ ሊያስቆጥሩ ሲሉ በተከላካዮች ኳስ በእጅ ተመልሶባቸው የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ ሬድዋን ናስር ቢመታውም የግብ ዘቡ ዮሐንስ በዛብህ አምክኖበታል። ምናልባት ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት የቀሩት ተጫዋቾቹም በ83ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያደርግ በነበረው አላዛር አማካኝነት የጅማን መረብ በማግኘት የማስተዛዘኛ ጎል ለማግኘት ጥረው ነበር። ነገርግን ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በጅማ ሁለት ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

የጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተመረጠው የጅማ አባጅፋሩ አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ ደግሞ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የዋንጫ እና የ12 ሺ ብር ሽልማቱን ተቀብሏል።