ሲዳማ ቡና ጋናዊ ተከላካይ አስፈረመ

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ሲዳማ ቡና ጋናዊውን የመሐል ተከላካይ በአንድ ዓመት ውል አስፈረመ።

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በማገባደድ በዛሬው ዕለት በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ራሱን ለመፈተሽ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አድርጎ 3ለ2 ማሸነፍ የቻለው ሲዳማ ቡና ጋናዊው የመሐል ተከላካይ ያኩቡ መሐመድን በአንድ ዓመት ውል በዛሬው ዕለት እንዳስፈረመ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

የክለብ ህይወቱን በትውልድ ሀገሩ ክለብ ሬድቡል ጋና በተባለ ቡድን የጀመረው ይህ የመሀል ተከላካይ በመቀጠል ዲ ኢንተርናሽናል እና አሻንቲ ጎልድ ክለቦች ውስጥም ቆይታን በማድረግ በመቀጠል ወደ ሞሮኮ አምርቶ ዩኒየን ኢት እንዲሁም ራጃ ካዛብላካ ግልጋሎትን መስጠት ችሏል፡፡ በመቀጠል ወደ ሀገሩ ጋና በድጋሚ በመመለስ አዱዋና ስታር ተጫውቶ ከ2016 ጀምሮ ለታንዛኒያው አዛም ክለብ ያለፉትን አምስት ዓመታት ከተጫወተ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለሲዳማ ቡና የአንድ ዓመት ውል ተፈራርሟል፡፡