የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የብሄራዊ ቡድኑን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ አመሻሹ ላይ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ተካሂዷል፡፡ ጭቅጭቆች እና ስሜታዊ ንግሮች በተስተዋሉበት የዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ረዳታቸው ፋሲል ተካልኝ እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ አሊ ረዲ ተገኝተዋል፡፡ በመግለጫው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የሰጧቸውን ምላሾች እና ማብራርያዎች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ስለ ምርጫው
24 ተጫዋች መምረጥ ያስፈለገው ተጫዋቾች ቢጎዱ እንኳ ውድድሮች ስለሌሉ ተጫዋቾችን ከእረፍት መጥራት አዳጋች በመሆኑ ነው፡፡
በየቦታው ቢያንስ 2 ተጫዋቾች የመረጥን ሲሆን አንዳንዶቹ 3 ቦታዎች መጫወት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሞገስ ፣ በረከት እና ግርማ በተለያዩ የተከላካይ ሚናዎች መጫወት ይችላሉ፡፡
የመረጥነው በተነገረን ፣ በደጋፊ ወይም በመደለል ሳይሆን ከተጫዋቾቹ ተጨባጭ አቋም ተነስተን ነው፡፡ አንዳንዶች ጨዋታ ያላደረጉ ተጫዋቾችን ከቤት ጠርታችሁ አምጧቸው ብለውናል፡፡ ከአንድ ክለብ ውጪ ከሁሉም የሊጉ ክለቦች ተመርጠዋል ተብለናል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ የምመርጠው በኮታ ሳይሆን በብቃታቸው ነው፡፡ ተጫዋችን ለመምረጥ መስፈርት ያስፈልጋል፡፡ ባሬቶ ወይም ሰውነት ስለመረጡት እኔ ልመርጠው አልችልም፡፡
ይህንን የመለያ ጨዋታ ባናደርግ ኖሮ ከነጉዳታቸው የምንመርጣቸው ተጫዋቾች ይኖሩ ነበር፡፡
የተጎዱት ተጫዋቾች በልምምድ ጨዋታው ላይ ሳይሆን ከመጀመርያው ጉዳት ይዘው የመጡ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ለአለም እና አብዱልከሪም የመጡት የመመረጥ እድሉን ስላገኙ ለማመስገንና በጉዳት መጫወት እንደማይችሉ ለማሳወቅ ነው የመጡት፡፡ የትራንስፖርት ወጪያቸውን ራሱ የሸፈኑት ራሳቸው ናቸው፡፡
ስለተጫዋቾች ጉዳት
ልምምድ ላይ ተጫዋቾች እንደተጎዱ የተነገረው ወሬ አሳዝኖኛል፡፡ ከሙሉአለም ውጪ በጨዋታዎቹ ላይ ግጭት ደርሶበት የተጎዳ ተጫዋች አልነበረም፡፡ አስራት ከመጀመርያው ተጎድቶ ነው የመጣው፡፡ በሜዳ ላይ ጥቂት ደቂቃዎች እንደቆየ ከማንም ጋር ሳይጋጭ ነው ጉዳቱ ያገረሸበት፡፡ የልምምድ ጨዋታውን ሳይከታተሉ የሚናገሩ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ በጭራሽ ጨዋታው ላይ ያልተሳፉ ተጨጫዋቾች ልምምድ ላይ ተጎዱ ብለው የሚያወሩ ጋዜጠኞችም አሉ፡፡
የተቀነሱት ተጫዋቾች
የተቀነሱት ተጫዋቾች አመስግነው ተለያይተዋል፡፡ አግባብ በሆነ መንገድ ስለተቀነሱ ቅሬታ አላቀረቡም፡፡ ከቀድሞ ክለቤ ደደቢት ከተመረጡት 7 ተጫዋቾች ሶስቱ ብቁ ስላልሆኑ ቀንሻቸዋልሁ፡፡ ይህ ራሱ የምርጫው አካሄድ በሚያሳዩት አቋም ላይ ብቻ መመስረቱን ያመላክታል፡፡
የወዳጅነት ጨዋታው እና እቅዶቻቸው
በወዳጅነት ጨዋታው የብሄራዊ ቡድኑ ቋሚ ተሰላፊዎችን ከመለየት ባሻገር የብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾችን ልምድ እንዲያገኙ እንጠቀምበታልን፡፡ እኔ እና ረዳቶቼ ለብሄራዊ ቡድን በመጫወታችን ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ምንያህል እንደሚያስደነግጥ እና ስሜት ውስጥ እንደሚከት እናውቀዋለን፡፡አንዳንድ ተጨዋቾች ደግሞ በጥቂት ተመልካቾች ፊት መጫወት የለመዱ በመሆናቸው ብዙዎች ትኩረት በሚሰጡት ብሄራዊ ቡድን ውስጥ በከፍተኛ ተመልካች ፊት መጫወትን አልለመዱም፡፡
እንደ እቅድ አስቀምጠን እየሰራን ያለነው የአጭር ጊዜ እቅድ ነው፡፡ ትኩረት አድረገን እየሰራን ያለነውም ከኬንያ ጋር እስከምናደርገው የመልስ ጨዋታ ያለውን ጊዜ ነው፡፡
ስለ ዋሊድ አታ እና ውጪ የሚገኙ ተጫዋቾች
ዋሊድን በስልክ አናግሬዋለሁ፡፡ቱርክ በህክምና ላይ ነው፡፡ ለቡድኑ ጨዋታዎች ስላላደረገ እዚህ መጥቶ ቢጎዳ ነገሮች እንደሚወሳሰቡ ገልፆልኛል፡፡ ከዛ ውጪ የብሄራዊ ቡድኑ ጥሪ ቀርቦለት አልመጣም ያለ ተጫዋች የለም፡፡ ኡመድ እና ሽመልስ ሰኞ ይገባሉ፡፡ ጌታነህ ሃገር ውስጥ ስላለ ለመገናኘት እየሞከርን ነው፡፡ ሳላዲን ጨዋታ ስላለበት ጨርሶ ይመጣል፡፡
በጉዳት ስለተቀነሱ ተጫዋቾች
በጉዳት ዝርዝር ውስት መግባት ካልቻሉት ተጫዋቾች መካከል ሶስት ተጫዋቾችን 24 ውስጥ ለማካተት አስበን ነበር፡፡ አስራት ፣ አብዱልከሪም እና ሙሉአለም በመጎዳታቸው 24 ውስጥ ልናካትታቸው አልቻልንም፡፡ በምትካቸውም ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ሞገስ ታደሰ እና ዮናታን ከበደን አካተናል፡፡
ከጋዜጠኞች ጋር ስላላቸው ግንኙነት
ከጋዜጠኞች ጋር ያለኝ ግንኙነት 98 በመቶ ጥሩ ነው፡፡ የሚሰማኝን እናገራለሁ ፣ የጋዜጠኞችን መብት የማከብረውን ያህል የእኔንም መብት አላስነካም፡፡ 1 እና 2 በመቶ ከሚሆኑት ጋር ግን ጥሩ ግንኙንነት የለኝም፡፡ የሚያጣላን ደግሞ እውነትን ባለመያዛቸው ነው፡፡ ውሸቶችን በማውራታቸው ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃዎች አሉኝ፡፡ ስለኳስ የሚያወራኝን አወራዋለሁ፡፡ አጀንዳ ቀይሮ ስለሌላ የሚያወራኝን ግን አላስተናግድም፡፡
ተጫዋቾችቻን የሚጫወቱት ጨዋታ ብዛት
የሃገራችን ተጫዋቾች መጫወት የሚገባቸውን ያህል የጨዋታ ብዛት እየተጫወቱ አይደለም፡፡ በፊፋ ስታንደርድ መሰረት እድሜው ከ17 አመት በታች ያለ ተጫዋች እንኳ መቻወት የሚገባው ከ30 ጨዋታ ያላነሰ ነው፡፡ ተጫዋቾቻችን ደካማ አቋም እንዲኖራቸው የሚያደርጋቸው የጨዋታ ጫና በዝቶባቸው ሳይሆን ጠንክረው ስለማይሰሩ ነው፡፡