የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከዛሬው የዛምቢያ ሽንፈት በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሰልጣኙ የሰጡት አስተያየት ከዚህ እነደሚከተለው ነው፡፡
ስለ ጨዋታው
‹‹ በመጀመሪያው ግማሽ የአማካይ ክፍሉ ተሰብሯል፡፡ ምክንያቱም አማካዮቹ ጋቶች እና ምንተስኖት ያልናቸውን አልተገበሩም፡፡ ሁለቱም ወደፊት በመንቀሳቀስ ግብ የማስቆጠር ጉጉት ነበራቸው፡፡ ስለዚህ መፍትኄ የነበረው አማካዮችን መለወጥ ነበር፡፡ ብሩክ እና ፍሬው ሲገቡ ጨዋታው ተለውጧል፡፡ አሁን ደግሞ ልምምዳችን እየተሻሻለ ሲመጣ ተጨዋቾቹ የመቀበል ፍላጎታቸውም ከፍተኛ ስለሆነ ስህተቶቻችንን በሚገባ እናርማለን፡፡ ››
አዳዲስ ተጫዋቾች
‹‹ ከቡድኔ ማየት የምፈልገውን ነገር እየየሁ ነው፡፡ ለዚህም ብለን አዳዲሶቹን ልጆች ተጠቅመናል፡፡ ልምድ የሚባለውን ነገር በተግባር እያዩት ነው፡፡ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ቀላል እንዳልሆነና ዝም ብሎ ገብቶ መጫወት እንዳማይችል ተረድተዋል፡፡ የህዝብ ጫና ፣ የሚዲያ ጫና ፣ የተጋጣሚ ቡድን ጫና እንዲሁም የምንገጥመው ቡድን አቋም እና መሰል ነገሮች ልምድ የሌላቸው ተጨዋቾች በኃልዮት ሳይሆን በተግባር ማየት ስለነበረባቸው ነባሮቹን እና ልምድ ያላቸውን አስቀምጠን እነዚህን ደግሞ ማየት ስለነበረብን አይተናል፡፡ በአውሮፓ የሚጫወቱ በነ ቲፒ ማዜምቤ እና ሳውዝሃምፕተን ከሚጫወቱ ልጆች ጋር ሲጫወቱ አቋማቸው ምን እንደሚመስል ማየት ነበረብን፡፡ ከዚህ አንፃር ስንገመግመው ጥሩ ነገር ዓይተናል ነው የምንለው፡፡ ምክንያቱም ለመጀመሪያው የሌሴቶ ጨዋታ 7 ወይም 8 ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን አሉን፡፡ ከዛ በኃላ ቻን ይመጣል፡፡ ቻን ላይ ደግሞ መጠቀም የምንችለው እነዚህን ተጫዋቾች ነው፡፡ ስለዚህም ምንም ልምድ ሳንሰጣቸው የሚገቡ ከሆነ ጥሩ አይሆንም፡፡ እንደነ አስቻለው፣ ዘካሪያስ፣ ሙጂብ እና ሁለቱ ግብ ጠባቂዎች ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ብዙ አልጠበቅንባቸውም፡፡ ነገር ግን ከጠበቅነው በላይ ጥሩ ነገር አሳይተውናል፡፡ እንደነባዬ ካሉተጫዋቾች ደግሞ የተበቅነውን አላገኘንም፡፡ ይህም ከልምድ ማነስ ነው፡፡ እንደውም ልምድ ካላቸው ከነ በኃይሉ አሰፋ የምንፈልገውን አላገኘንም፡፡
የአጥቂ ችግር
ከሌሴቶ ጋር በምናደርገው ጨዋታ ግማሽ በግማሽ አዲስ ቡድን ነው የምናየው፡፡ ትንሽ እንጠቀማለን ብለን የምናስበው ያለብንን የአጥቂ መስመር ችግር በሳላዲን ፣ ኡመድ እና ጌታነህ መምጣት እንቀርፈዋለን ብለን ነው፡፡
ስለወደፊት እቅዳቸው
እኔ የምፈልገው አሁን የያዝኩትን ብድን መገንባት እንጂ ለምንያህል ጊዜ እንደምቆይ ስለማላውቅ የረጅም ጊዜ እቅድ ሊኖረኝ አይችልም፡፡ ጠንካራ የእግርኳስ ትውልድ የሚገነባው በወር በሳምንት ሳይሆን በዓመታት ነው፡፡ አሁን የምሰራው የተሰጠኝን አደራ ለመወጣት ነው፡፡