“የህዝባችንን ክብር ዳግመኛ ለማግኘት ኢትዮጵያን ማሸነፍ አለብን።” – ማቡቲ ፖትሎዋኔ

የሌሴቶ ብሄራዊ ቡድን እና የማትላማ ክለብ የመሃል ሜዳ ስፍራ ተጫዋች ማቡቲ ፖትሎዋኔ እሁድ በባህርዳር ስታዲየም በሚደረገው ጨዋታ የቡድን ጓደኞቹ ያላቸውን አቅም በሙሉ አውጥተው እንዲታገሉ ጥሪውን አስተላልፏል።

የ2013/14 የሌሴቶ ፕሪምየር ሊግ የአመቱ ኮከብ ተጫዋች ስያሜን በማግኘት ያጠናቀቀው ፖትሎዋኔ በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት እና ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ዙርያ አስተያየቱን ሰጥቷል።

“የቡድን መንፈሳችን ጠንካራ ነው፤ በጥሩ ሞራል ላይ እንገኛለን። እንደ ቡድን የምናደርገው እንቅስቃሴም ጥሩ ነው። ከኢትዮጵያ ጋር በምናደርገው ጨዋታም የሃገራችንን ህዝብ የሚያኮራ ውጤት እናስመዘግባለን። ከኢትዮጵያ ጋር ባለን ጨዋታ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንፈልጋለን።”

“እኛ እንደ እግርኳስ ተጫዋች በርካታ ህልሞች አሉን። የአፍሪካ እና የዓለም ዋንጫን በመሳሰሉ ታላላቅ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ በመሆን ለሃገራችን አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ እንፈልጋለን። በአሁኑ ሰዓት ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ቻን) ማለፍ እቅዳችን ነው።”

ፖትሎዋኔ የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የደቡብ አፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ኮሳፋ) ላይ ስላስመዘገበው አመርቂ ያልሆነ ውጤት ተጠይቆ “በኮሳፋ ነገሮች እንዳሰብናቸው ሊሄዱልን አልቻሉም ነበር። ከውድድሩ በኋላ ድክመቶቻችንን ለማረም እየጣርን እንገኛለን። ጠንካራ እና ደካማ ጎናችንን ለመለየትም ውድድሩ በእጅጉ ጠቅሞናል። የህዝባችንን ክብር በድጋሚ ለማግኘት ኢትዮጵያን ማሸነፍ ግድ ይለናል፤” በማለት መልሷል። ሌሴቶ በ2015ቱ የኮሳፋ ዋንጫ በማዳጋስካር 2-1 እና በስዋዚላንድ 2-0 ተሸንፋ ታንዛንያን በመጨረሻው ጨዋታ 1-0 በማሸነፍ ከምድቡ ተሰናባች እንደነበረች ይታወሳል።

በቅርቡ በሌሴቶ እግርኳስ በተደጋጋሚ ያጋጠመውን የተጫዋቾች እና የእግርኳስ ማህበሩ በተጫዋች ጥቅማጥቅም ዙርያ አለመስማማት አሁን በመፈታቱ ተጫዋቾቹ ትኩረታቸውን ሰብስበው እንዲዘጋጁ እንደረዳቸው ፖሎትዋኔ ይናገራል። “ከሌሴቶ እግርኳስ ማህበር ጋር ከስምምነት ላይ ደርሰናል። ባቀረቡልን የጨዋታ ጉርሻ መጠንም ደስተኛ ነን።”

የሌሴቶ እግርኳስ ማህበር ዋና ፀሃፊ ሞኮሲ ሞሃፒ የተጫዋቾች የቀን አበል ቀድሞ ከነበረበት በቀን 150 ሎቲ (የሌሴቶ ገንዘብ) ወደ 200 ሎቲ (ወደ 350 ብር መሆኑ ነው) እንዲያድግ መደረጉን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እና ሌሴቶ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ እሁድ ከቀኑ በ10 ሰዓት በግዙፉ ባህርዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ይደረጋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *