“ለኛ ትልቁ ስጋት ኢትዮጵያ ሳትሆን የአፍሪካ ምርጥ ቡድን የሆነችው አልጄሪያ ነች” – የሌሴቶ አሠልጣኝ ሲፌፌ ማቴቴ

የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሲፌፌ ማቴቴ ቡድናቸው ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ እሁድ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ እንደሚኖርበት ገልፀዋል።

“ባለፈው ወር በተሳተፍንበት የኮሳፋ ዋንጫ በመጀመሪያው ጨዋታ በማዳጋስካር በመሸነፋችን ምክንያት ችግር ውስጥ ገብተን ነበር። በዚህም ምክንያት ከምድቡ ማለፍ ሳንችል ቀርተናል። በዚህ ምክንያት ነው አሁን በመጀመሪያ ጨዋታችን ኢትዮጵያን ማሸነፍ አስፈላጊያችን ነው ብዬ የምናገረው። ይህንን ጨዋታ ብናሸንፍ የምናገኘው በራስ መተማመን ወደፊት ለሚጠብቁን ጨዋታዎች ስለሚጠቅመን ለኛ ወሳኝ ጨዋታ ነው። ከኮሳፋ ጋር ተመሳሳይ ነገር እንዲገጥመን አንፈልግም፤ ይህንንም ለተጫዋቾቼ አስረግጬ ነግሬያቸዋለሁ።”

የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን በ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 ከኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ እና ሲሼልስ ጋር ተደልድሏል።

“ከባድ ምድብ ውስጥ እንገኛለን። ነገር ግን ለኛ ትልቁ ስጋት ኢትዮጵያ ሳትሆን የአፍሪካ ምርጥ ቡድን የሆነችው አልጄሪያ ነች። በዚህ ምክንያት ነው ምድቡን አልጄሪያን ተከትለን ቢያንስ በሁለተኝነት ለማጠናቀቅ ያቀድነው። ነገርግን ይህ እግርኳስ ነው እና ምድቡን በመሪነት አጠናቀን በቀጥታ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ልናልፍ የምንችልበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል።”

ማቴቴ አያይዞም ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ቀላል ፈተና እንደማይጠብቀው ተናግሯል።

“እጅግ ወሳኝ እና ከባድ ጨዋታ ይጠብቀናል፤ ምክንያቱም ባለሜዳነቱን ተጠቅሞ ሙሉ 3 ነጥብ ለማግኘት ከሚጥር ጥሩ ቡድን ጋር ነው የምንጫወተው። ለዚህም ነው ትኩረታችንን በሙሉ ጨዋታው ላይ በማድረግ ከባህርዳር ጥሩ ውጤት ይዘን መመለስ አለብን ብዬ የምናገረው።”

ሲፌፌ ማቴቴ የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሠልጣኝነት ሲረከብ ቡድኑን በኮሳፋ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ማስገባት እና ሩዋንዳ ላይ ለሚደረገው የ2016 ቻን ዋንጫ የማሳለፍ ሃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም በኮሳፋ ቡድኑ ከምድብ ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ነገርግን ማቴቴ ከአሠልጣኝነቱ እንደማይነሳ እና በቻን ማጣሪያ ላይ የሚያስመዘግበው ውጤት ታይቶ የወደፊት ጉዞው እንደሚወሰን የሌሴቶ እግርኳስ ማኅበር ማሳወቁ ይታወሳል።

እ.ኤ.አ. ከ1974 ዓ.ም. ጀምሮ በማጣሪያ ውድድሮች እየተሳተፈ የሚገኘው የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን አንድም ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ አልቻለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *