ቻምፒየንስ ሊግ| የመጨረሻ ምድብ ጨዋታዎች ቅዳሜ ይጀመራሉ

የ2017 ቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ነገ መደረግ ይጀምራሉ፡፡ ኤትዋል ደ ሳህል፣ ኤስፔራንስ እና የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ወደ ሩብ ፍፃሜ መግባታቸውን ያረጋገጡ ሶስት ክለቦች ሲሆን ከቅዳሜ ጀምሮ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ቀሪ አላፊ ክለቦችን ይታወቃሉ፡፡

ፊፋ ሱዳንን ከማንኛውንም አይነት የእግርኳስ እንቅስቃሴ ሐሙስ ማምሻውን ማገዱን ተከትሎ ከምድብ የማለፍ ተስፋ የነበረውን ኤል ሜሪክን አጨልሟል፡፡ የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምድብ መሰናበቱን ባሳለፍነው ሳምንት ቢያረጋግጥም ምድቡን በሶስተኛ ደረጃ በማጠናቀቅ የገንዘብ ሽልማት መጠኑን እንዲሁም በካፍ የክለቦች ደረጃ አወጣጥ የሚያገኘውን ነጥብ ለማሳደግ በማለም ወደ ቱኒዚያ ሐሙስ አምርቷል፡፡

 

ምድብ 1

ኤትዋል ደ ሳህል አስቀድሞ ማለፉን ባረጋገጠበት ምድብ የሞዛምቢኩ የፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ ፊፋን ሱዳንን ተከትሎ ከምድቡ አላፊ ሁኗል፡፡ ከምድቡ የማለፉ ነገር በጣም አነስተኛ የነበረው ክለቡ ባልታሰበ ሁኔታ የሩብ ፍፃሜ ትኬቱን ቆርጧል፡፡ አል ሂላል ከምድብ አስቀድሞ መሰናበቱን ያረጋገጠ ሲሆን የመንግስት ጣልቃ ገብነትን ተከትሎ ሱዳን ከእግርኳስ መታገዷን ተከትሎ ኤል ሜሪክ ከምድቡ ተሰናብች ሆኗል፡፡ ውሳኔው እስከዛሬ ከሰዓት የማይለወጥ ከሆነ በዚሁ ምድብ የሚደረገው የኤትዋል ደ ሳህል እና ኤል ሜሪክ እንደሚሁም የአል ሂላል እና ፌሮቫያሪዮ ቤይራ ጨዋታ በእገዳው ምክንያት አይካሄድም፡፡ በያዝነው የውድድር አመት በተመሳሳይ ማሊ ከፊፋ እገዳ ተጥሎባት ሁለቱ ክለቦቿ አንዜ ክሬቸርስ እንዲሁም ጆሊባ ባማኮ ከውድድር መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡

 

ምድብ 2

በዚህ ምደብ አላፊ ክለቦች ያልታወቁ ሲሆን ዩኤስኤም አልጀር እና አል አሃሊ ትሪፖሊ የማለፍ የተሻለ እድልን ይዘዋል፡፡ ምድቡን ዩኤስኤም አልጀር እና አል አሃሊ ትሪፖሊ በ8 ነጥብ ሲመሩ ካፕስ ዩናይትድ በ6 እንዲሁም ዛማሌክ በ5 ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ እሁድ በሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች አሰልጣኝ ኢናሲዮን በካፕስ ዩናይትድ ሃራሬ ላይ ከተሸነፈ በኃላ ያሰናበተው እና የማለፍ እድሉ እየጠበበ የመጣው የአምስት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ ዛማሌክ አል አሃሊ ትሪፖሊን ያስተናግዳል፡፡ የግብፅ መንግስት 12500 የዛማሌክ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም ገብተው ክለባቸውን እንዲያበረታቱ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ በሌላኛው ጨዋታ አልጀርስ ላይ ዩኤስኤም አልጀር ካፕስ ዩናይትድን ይገጥማል፡፡ አቻ መውጣት ለዩኤስኤም አልጀር እና አሃሊ ትሪፖሊ በቂ ሲሆን ካፕስ ዩናይትድ እና ዛማሌክ ያለባቸውን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ጨዋታቸውን ይጀምራሉ፡፡

 

ምድብ 3

በዚህ ምድቡ አላፈ ክለቦች ባሳለፍነው ሳምንት መታወቃቸውን ተከትሎ በኤስፔራንስ እና ማሜሎዲ ሰንዳውንስ መካከል ምድቡን በአሸነፊነት ለማጠናቀቅ ከሚደረገው ፉክክር ይበልጥ ከፍተኛ ስፍራ ይይዛል፡፡ የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤስፔራንስ ጋር ላለበት ጨዋታ ወደ ቱኒዝ ሐሙስ አቅንቷል፡፡ ቅጣቱን የጨረሰው ሳላዲን በርጌቾ ጉዳት ላይ በመገኘቱ ከጨዋታው ውጪ ነው፡፡ ፈረሰኞቹ በሰንዳውንስ ተሸንፈው ከውድድሩ ቢሰናበቱም ምድቡን በሶስተኛ ደረጃ በማጠናቀቅ የገንዘብ ሽልማት መጠኑን እንዲሁም በካፍ የክለቦች ደረጃ አወጣጥ የሚያገኘውን ነጥብ ለማሳደግ የእሁዱ ጨዋታ ይጠቅመዋል፡፡ በሌላኛው የምድብ ጨዋታ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከኤኤስ ቪታ ክለብ ፕሪቶሪያ ላይ ይጫወታሉ፡፡

 

ምድብ 4

አላፊ ክለቦች ልክ እንደምድብ 2 ያልታወቁበት ምድብ ነው፡፡ ሶስት ክለቦች ለሩብ ፍፃሜ ቦታ እየተፋለሙ ሲገኝ የካሜሮኑ ኮተን ስፖርት ከቻምፒየንስ ሊግ አስቀድሞ የመሰናበቱን አረጋግጧል፡፡ ዋይዳድ ካዛብላንካ የምድብ መሪውን ዛናኮን ሲገጥም አል አሃሊ በሜዳው ኮተን ስፖርትን ያስተናግዳል፡፡ ምድቡን ዛናኮ በ11 ነጥብ ሲመራ ዋይዳድ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው፡፡ ባለሪከርድ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አሃሊ 8 ነጥብ አለው፡፡ ዋይዳድ ማሸነፍ የሚችል ከሆነ ምድቡን በአሸናፊነት ማለፉን የሚያረጋግጥ ሲሆን አል አሃሊ ድል ከቀናው ከዛናኮ ጋር በነጥብ ይስተካከላል፡፡ ሁለቱ ክለቦች እርስበእርስ ተገናኝተው ያለግብ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን መጨረሳቸውን ተከትሎ ከምድብ አላፊ ክለቡን ለመለየት የግብ ክፍያቸው ይታያል፡፡ ዛናኮ የመጨረሻ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ሞሮኮ ላይ ማድረጉት ተከትሎ እንዲሁም አል አሃሊ በሜዳው በውድድሩ ደካማ አቋም ያሳየውን ኮተንን መግጠሙ አሃሊ የተሻለ የማለፍ ቅድመ ግምትን እንዲሰጠው አድርጓል፡፡

 

አርብ መካሄድ የነበረባቸው ሁለት ጨዋታዎች ሱዳን በፊፋ በመቀጣቷ ምክንያት አይደረጉም፡፡ ኤትዋል ደ ሳህል እና ፌሮቫያሪዮ ቤይራ ከምደብ አንድ አልፈዋል፡፡

 

የቅዳሜ ጨዋታ

19፡00 – ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ ከ ዛናኮ (ስታደ ኮምፕሌክስ መሃመድ አምስተኛ)

21፡0 – አል አሃሊ ከ ኮተን ስፖርት (ቦርግ ኤል አረብ ስታዲየም)

 

የእሁድ ጨዋታ

18፡00 – ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)

19፡00 – ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ ኤኤስ ቪታ ክለብ (ሉካስ ማስተርፒስስ ሞሪፔ ስታዲየም)

20፡00 – ዩኤስኤም አልጀር ከ ካፕስ ዩናይትድ (ስታደ ጁላይ 5 1962)

21፡00 – ዛማሌክ ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ፔትሮ ስፖርት ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *