አሰልጣኝ መኮንን ስለ ጅማ ከተማ ስኬታማ የውድድር አመት ይናገራሉ 

በሁለት ምድቦች ተከፍሎ በቀጣይ አመት ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያልፉትን ክለቦች ለመለየት ሲደረጉ የነበሩት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኞ  ሲጠናቀቅ ጅማ ከተማም ወልቂጤ ከተማ ላይ የ3-1 ድል ካስመዘግበ በኃላ በቀጣይ አመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ተሳታፊ መሆኑን ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ መኮንን ሀብተዮሀንስ ስላሳለፉት የከፍተኛ ሊግ ውጣ ውረድ እና ስለ ክለባቸው የስኬት ሚስጥር ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት እና ዳሽን ቢራን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሳድገዋል፡፡ አሁን ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ ጅማ ከተማን አሳድገዋል፡፡ በአጠቃላይ ከድሉ በኃላ ምን ተሰማዎት?

በጣም ደስ ይላል፡፡ ሶስት ጊዜ ሲባል ቁጥሯ ትንሽ ትመስላለች፡፡ ነገር ግን በጣም ከባድ ጊዜያትን አሳልፌለሁ፡፡ በዚህም ቡድን እንዲሁም ከዚህ ቀደም በነበርኩባቸው ክለቦች አላማን እንደማሳካት የሚያስደስት ነገር የለም እና እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ የክበሉን ደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

የስኬታችሁ ሚስጥር ምን ነበር? አንተስ ወደ ቡድኑን ከሁለተኛው አጋማሽ የውድድር ዘመን በኃላ ከመጣህ ጀምሮ  ምን ምን ለውጦችን አደረክ?

እኔ የውድድሩ አጋማሽ ላይ ነው የመጣሁት፡፡ ቡድኑ ከኔ በፊት የነበረውን እንቅስቃሴ በጥልቀት አላውቅም ነበር ፤ ግን ቡድኑን ስረከበው እና እንዲሁ በወሬ የምሰማው ቡድኑ የአመጋብ እንዲሁም 90 ደቂቃ በሙሉ አቅም የመጫወት ችግሮች እንዳሉበት ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ላይ ብዙ ስራዎችን ከአሰልጣኝ ቡድኑ እና ከቡድኑ አመራሮች ጋር ተባብረን ለመስራት ሞክረናል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ገና ሁለተኛ አመቱ ነው፡፡ ብዙ ፈታኝ ነገሮች እንዳሉት ብዙዎች ይኛገራሉ፡፡ በአንተስ እይታ ፈታኝ ነገሮቹ ምን ምን ነበሩ ትላለህ?

እውነት ነው በጣም ፈታኝ ነገሮች አሉበት፡፡ ጨዋታዎችን ለማድረግ በጣም ረጃጅም ጉዞዎችን ነበር የምናደርገው ፤  ለዛውም በመኪና፡፡ ይህ ደግሞ የተጨዋቾቹ አቋም ላይ አሉታዊ ተፅኖ ያመጣል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የምግብ ጉዳይ ራሱ ሌላ ራስ ምታት ነበር፡፡ አንድ ስፖርተኛ ግዴታ ከልምምድ እና ከጨዋታ መልስ ያወጣውን ጉልበት መተካት አለበት፡፡ ለእንደዚህ አይነት ነገሮች ግን ከምናደርጋቸው ረጃጅም ጉዞዎች አንፃር በጣም ከባድ ነበር፡፡ እንደፈለግን ተጨዋቾቻችንን በዚህ ረገድ አላዘጋጀንም፡፡ ሌላው የሜዳዎች አለመመቸት ነው፡፡ ብዙ ለጨዋታ ብቁ ባልሆኑ ሜዳዎች ላይ ተጫውተናል፡፡ እነዛ ምቹ ያልሆኑ ሜዳዎች ደግሞ ያሰብከውን ነገር ጨዋታው ላይ እድትተገብር አያደርጉህም ፤ አልፎ ተርፎ ተጨዋቾቻችን ሲጎዱብን ነው የምትመለከተው እና የሜዳዎች ችግር ከፍተኛ ነበር፡፡ የዝግጅት እና የእረፍት ጊዜያት ማጠር እንዲሁም ሌሎችም ውድድሩን ፈታኝ አድርገውብን ነበር፡፡

ከክለቡ አመራሮችስ በኩል በቂ ድጋፍ ይደረግላችሁ ነበር?

እውነት ለመናገር የክለቡ አመራሮች በጣም ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል፡፡ አንድ ቡድን በተጫዋቾች ወይንም በአሰልጣኙ ጉብዝና ብቻ ስኬት አያመጣም፡፡ ግዴታ አስተዳደራዊ ጉዳዮችም የተረጋጉ እና እግር ኳሱን የሚያጠናክሩ መሆን አለባቸው፡፡ የጅማ ከተማ የክለብ አመራሮች ደግሞ ይሄንን ነገር በሚገባ ሲያደርጉት ነበር፡፡ ተጨዋቾችን ለማበረታታት የተለያዩ መንገዶችን (ኢንሴንቲቭን ጨምሮ) ይጠቀሙ ነበር፡፡ ቡድኑ በከፍተኛ ሞራል እንዲጫወት ከጎናችን ሆነው ሲደግፉን ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ነገር እጅግ ደስተኛ ነኝ እነሱም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

የቡድኑ ደጋፊዎች የሜዳ ላይ ጨዋታዎችን ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ቦታው ላይ በመገኘት ቡድኑን ሲያበረታታ ታዝበናል፡፡ ስለደጋፊዎቹስ ምን ትላለህ?

ደጋፊዎቹ እጅግ በጣም የሚገርሙ ናቸው፡፡ በየጨዋታዎቻችን ያበረታቱን ነበር፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት የቡድኑ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ እነዚህም ደጋፊዎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ነገር ግን ሊሻሻሉ የሚገባቸው ነገሮችን ቶሎ ተነጋግረን ለቀጣይ አመት ማሻሻል አለብን፡፡ ውጤት ሲመጣ ብቻ ሳይሆን ውጤት ሲጠፋም ከጎናችን ሆነው አይዟችሁ ሊሉን ይገባል፡፡

በቀጣይ አመትስ ከቡድኑ ጋር አብረህ ትቆያለህ?

እርግጥ ውሌ በዚህኛው የውድድር ዓመት ያልቃል፡፡ ነገር ግን የቀጣይ አመት ቆይታዬ ከክለቡ አመራሮች ጋር በሚደረግ ንግግር የሚወሰን ይሆናል፡፡ እኔ ዋና የነበረብኝን ኃላፊነት (ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማስገባት) ፈጣሪ ይመስገን አሳክቼዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሲቪዬን ለማሳደግና አዳዲስ ፈተናዎችን መጋፈጥ እፈልጋለሁ፡፡ እንግዲህ የሚሆነውን አብረን ወደፊት እናያለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *