ኬንያ 2018፡ ኢትዮጵያ የቻን ማጣሪያዋን በድል ጀምራለች

ኬንያ በ2018 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) ለማለፍ በዞን ተከፋፍሎ የሚደረገው የማጣሪያ ዙር አርብ ሲጀመር ዛሬ ከሰዓት ጅቡቲን ከሜዳው ውጪ የገጠመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 5-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ የፊት አጥቂው ጌታነህ ከበደ አራት ግቦችን በጨዋታው ላይ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጋና 5-0 ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ የስድስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ነበር አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ወደ ጨዋታው የገቡት፡፡ ተከላካዩ ደስታ ዩሃንስ፣ አማካዮቹ ታፈሰ ሰለሞን እና ጋዲሳ መብራቴ እንዲሁም አጥቂው አብዱልራህማን ሙባረክ ጨዋታውን በቋሚነት መጀመር ችለዋል፡፡

ሱማሊያዊያን ዳኞችን በመሩት የኤል ሃጂ ሃሰን ጉሌድ ስታዲየም ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ እንግዶቹ በጌታነህ ተጨማሪ ሶስት ግቦች እና በሙሉአለም መስፍን ግብ 5-1 አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡

ጅቡቲ በአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከወራት በፊት ደቡብ ሱዳንን በሜዳዋ 2-0 ማሸነፍ ብትችልም የቀድሞ አሰልጣኟን ቱኒዚያዊውን ኑረዲን ጋርሳሊን ከመለሰች ወዲህ ወደ ለመደችው የሽንፈት ጉዞ ሄዳለች፡፡

ከ2007 ወዲህ አንድ ጨዋታ ብቻ ድል ያደረገው የጅቡቲ ብሄራዊ ቡድን በኢትዮጵያ መሸነፉ እምብዛም የሚገርም አይሆንም፡፡ ጅቡቲ ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በደቡብ ሱዳን 6-0 ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ ደካማ ብሄራዊ ቡድኖች ካሏቸው የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት መካከል በምትመደበው ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ መካከል የሚደረገው የመልስ ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ ሃምሌ 18 ሃዋሳ ላይ ይደረጋል፡፡ ጨዋታውን እንዲመሩ ካፍ ሱዳናዊያን ዳኞችን ሹሟል፡፡ አንድ እግሩን ወደ ቀጣዩ የመጨረሻ ዙር ያሻገሩት ዋሊያዎቹ በቀጣዩ ዙር የቡሩንዲ እና ሱዳንን አሸናፊ የመግጠም እድላቸው እጅጉን ጨምሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *