ወልዲያ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስን አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን ክስተት የነበረው ፋሲል ከተማን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ በሊጉ ጠንካራ የሆነ ቡድን መገንባት ቢችልም በሁለተኛው ዙር ቡድኑ ካጋጠመው መንሸራተት እና ህክምና ጋር በተያያዘ ከክለቡ ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ዘማሪም ወልደጊዮርጊስ ቀጣዩ የወልድያ አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

በአዳማ ከተማ ፣ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ እንዲሁም በሌሎች የሊጉ የታችኛው እርከን በሚገኙ ክለቦች የማሰልጠን ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ በፋሲል ከተማ በነበራው የሁለት አመት ከግማሽ ቆይታ ቡድኑ በ2007 የውድድር ዘመን ብሔራዊ ሊግ የምድቡ መሪ ሆኖ በማጠናቀቅ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማለፍ ድሬዳዋ ላይ በተደረገው የማጠቃለያ ውድድር ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የማለፍን ከፍተኛ ቅድመ ግምትን ቢያገኙም ወደ ሊጉ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በቀጣይም በ2008 የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጠንካራ ቡድን በመስራት ከምድብ ሀ ወልዲያን አስከትሎ ከ2000 የውድድር ዘመን በኃላ አፄዎቹ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲገቡ ከፍተኛ አስተዋፅኦን ተወጥቷል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም በፕሪምየር ሊጉ ከቡድኑ እስከተለያየበት ወቅት ፋሲል ከተማ ካደረገው አስደማሚ ጉዞ ጀርባ ጉልህ አስተዋጽኦን ተወጥቷል፡፡

አሰልጣኙ ከፋሲል ከተማ ከተለያዩበት ጊዜ አንስቶ ስማቸው በስፋት ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ቢቆይም በስተመጨረሻም መዳረሻቸው ወልዲያ ሆኗል፡፡ በዛሬው እለት ከክለቡ ጋር በተፈራረሙት ውል መሰረት ለቀጣይ ሁለት የውድድር ዘመናት ወልድያን የሚያሰለጥኑ ሲሆን ከሊጉ ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋዮች አንዱ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ወልዲያ በኢትዮጵያ ጥሎማለፍ ግማሽ ፍጻሜ በመከላከያ ከደረሰበት ሽንፈት በኃላ ከቀድሞው አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ጋር በስምምነት መለያየቱ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *