ሪፖርት | መቐለ ከተማ ፕሪምየር ሊጉን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ተቀላቅሏል

የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እጅግ ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ ድሬዳዋ ስታድየም ላይ ተደርጎ መቐለ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 በመርታት ለመጀመርያ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን ተቀላቅሏል፡፡

ይህን ወሳኝ ጨዋታ ለመከታተል በርካታ ተመልካች በድሬደዋ ስታድደም የታደመ ሲሆን በሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ታጅቦ ተካሂደል፡፡ በከተማው ከነበረው ከፍተኛ ሙቀት አንጻር በድንገት የጣለውና ጨዋታውን እስከማቋረጥ የደረሰው ዝናብም የጨዋታው አንድ ክስተት ነበር፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በጥሩ ብቃት በመራው የሁለቱ ቡድኖች ወሳኝ ጨዋታ 3ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ሁኔታ ጨዋታውን የጀመሩት ሀዲያዎ ሆሳዕናዎች ከማዕዘን ምት በተሻገረ ኳስ ጎል አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም ኳሱን ወደ ጎልነት የቀየረው አምረላ ደልታታ በግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ላይ ጥፋት ሰርቶ ሚዛን አስቶታል በሚል ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡ የሀድያ ተጠባባቂ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ጎሉ የፀደቀ መስሏቸው ደስታቸውን በአስገራሚ ሁኔታ ሲገልፁም ነበር።

ጨዋታው ቀጥሎ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት የተቋረጠ ሲሆን ከ12 ደቂቃዎች በኋላ ዝናቡ ማባራቱን ተከትሎ ከተቋረጠበት ቀጥሏል፡፡

በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴ ረገድ ተሽለው የቀረቡት ሀዲያዎች ጎል በማስቆጠርም ቀዳሚ ነበሩ፡፡ 14ኛው ደቂቃ ላይ በጉልበት እና ፍጥነት የመቐለ ከተማ ተከላካዮችን እረፍት ሲነሳ የነበረው እንዳለ ደባልቄ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሀድያ ሆሳዕናን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።

የሀዲያ የመሪነት ግብ የዘለቀው ለቅፅበት ብቻ ነበር፡፡ በስታድየም የነበረውና በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች ደስታውን ገልፆ ሳይጨርስ የከፍተኛ ሊጉ ክስተት አማኑኤል ገብረሚካኤል በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ላይ የግብ ጠባቂው አስራትን አቋቋም ተመልክቶ አክርሮ የመታው ኳስ ሀድያ መረብ ላይ አረፋ መቐለ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።

ጨዋታው በአስገራሚ የመሸናነፍ ፍላጎት እና እልህ ቀጥሎ ሀዲያዎች በፍጥኘት ወደ መሪነት ሊመለሱባቸው የሚችሉባቸውን እድሎች መፍጠር ችለው ነበር፡፡ በተለይ በ20ኛው ደቂቃ ላይ በእንዳለ ደባልቄ እንዲሁም አምረላ ደልታታ አማካኝነት አግኝተው ሶፎንያስ ሰይፋ በአስገራሚ ሁኔታ አድኖባቸዋል። በተጨማሪም በ27ኛው ደቂቃ በተከላካይ አማካያቸው አሚኑ ነስሮ አማካኝነት በግንባሩ ገጭቶ የመታው ኳስ ለጥቂት አግዳሚውን ታኮ ወደ ውጭ የወጣው ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡

በአንድ ሁለት ቅብብልም ሆነ በረጃጅም ኳሶች ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት ሀድያዎች ተጨማሪ የጎል እድል ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን መቐለዎችም የአማኑኤል ገ/ሚካኤልን የግል ጥረት ተጠቅመው አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

በ35 ኛው ደቂቃ ላይ መቐለ ከተማዎች በአምበሉ አሌክስ ተሰማ አማካኝነት ክስ ለማሲያዝ ሲሞክሩ የዕለቱ ዳኛ በአምላክ ተሰማ ጨዋታ ተቋርጦ ክስ ማስያዝ አይቻልም በማለት ጨዋታውን ማስቀጠላቸው የጨዋታው አንድ አጋጣሚ ነበር። የመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ 10 ደቂቃዎችም የጎል ሙከራዎች ሳይሰተናገዱበት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀላባ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ እንደነበረው ሁሉ አምበሉ ኄኖክ አርፊጮ እና ግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ ተገቢ ያልሆኑ ተጨዋቾች ናቸው በሚል ክስ በማስያዝ የጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ ቀዝቀዝ ባለ እና በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ሀድያ ሆሳዕናዎች ከመጀመርያው በወረደ መልኩ ተዳክመው ቀርበዋል፡፡ በአንጻሩ መቐለዎች ተሻሽለው ቀርበዋል፡፡

የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ የጎል ሙከራ ሳያስተናግድ እስከ 78ኛ ደቂቃ የዘለቀ ሲሆን በ78ኛው ደቂቃ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ዮሴፍ ኃይሉ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና የግብ ክልል የላከው ኳስ የግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞን የአቋቋም ስህተት ተከትሎ በቀጥታ ወደ ግብነት ተለውጧል፡፡ ጎሉም በስታድየሙ የነበሩት የመቐለ ደጋፊዎችን ወደ ጥልቅ ደስታ አሸጋግራለች፡፡

በቀሩት አስራ ሁለት ደቂቃዎች መቐለዎች ውጤቱን ለማስጠበቀ በጥብቅ መከላከል ኳሶችን ከግብ ክልላቸው በማራቅ ሲጠመዱ በአንፃሩ ሀዲያዎች በሙሉ አቅማቸው በመጠቀምና የአጥቂ አማራጫቸውን በማብዛት ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታው በመቐለ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ መቐለ ከተማ ጅማ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ተከትሎ ወደ 2010 የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ መቀላቀል ችሏል፡፡ በመቐለ ከተማም ቁጥሩ ከፍተኛ የሎነ የከተማው ህዝብ ወደ አደባባዮች በመውጣት ደስታውን በከፍተኛ ሁኔታ ሲገልፅ አምሽቷል፡፡

በ1965 የተመሰረተው መቐለ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት እየፈረሰ እና በድጋሚ እየተመሰረተ ቆይቶ በ2000 እንደአዲስ ከተመሰረተ ወዲህ በተለያዩ የታችኛው ሊግ እርከኖች ሲወዳደር ቆይቶ ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ አድጓል፡፡ ፕሪምየር ሊጉ እንደአዲስ ከተጀመረበት 1990 ወዲህ የተሳተፈ 48ኛው ክለብም መሆን ችሏል፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *