የከፍተኛ ሊጉ ክስተት አማኑኤል ገብረሚካኤል

በ2009 የኢትዮዽያ ከፍተኛ ሊግ በዘንድሮ የውድድር አመት ድንቅ አቋማቸውን ካሳዩና በቡድናቸው ውጤት ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ተጫዋቾች መካከል የመቐለ ከተማው አማኑኤል ገብረሚካኤል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

ትውልድ እና እድገቱ መተማ የሆነው አማኑኤል አምና በፈረሰው ዳሽን ቢራ ተስፋ ቡድን አልፎ እስከ ዋናው ቡድን መድረስ ቢችልም ብዙም የመሰለፍ እድል ባለማግኘቱ በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ወደ ነበረው ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሀን በ2008 የውድድር ዘመን ተዛውሮ ነበር፡፡ ሆኖም በደብረብርሀኑ ክለብ በተመሳሳይ የመሰለፍ እድል በማጣቱ ዘንድሮ መቐለ ከተማን ተቀላቅሎ የብዙዎች ትኩረት የሆነ የውድድር ዘመንን ማሳለፍ ችሏል፡፡
በትላንቱ የመለያ ጨዋታ ጨምሮ በውድድር ዘመኑ 18 ጎሎችን ያስቆጠረው አማኑኤል በርካታ ችግሮችን ተቋቁመው ለፕሪምየር ሊግ እንደበቁ ይናገራል፡፡ ” ውድድሩ ከባድ ነበር፡፡ ብዙ ችግሮችም ነበሩበት፡፡ ያም ቢሆን እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁመን ነው እዚህ መድረስ የቻልነው፡፡

” ከቡድኑ ጋር አብረን ነው የምንሰራው፡፡ በወሳኝ ሰአት የማገባቸው ጎሎች ለቡድኑ ወሳኝ ቢሆንም ሰልጣኛችን የሚሰጠንን ልምምድ ጠንክረን በመስራት እና በቡድናችን ውስጥ ያለው ፍቅር አንድነታችን ለዚህ ውጤት አብቅቶናል” በማለት ውጤቱ የእሱ ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን መስራታቸው መሆኑን ገልጿል፡፡


አምና የመሰለፍ እድል ያላገኘበት ሰሜን ሸዋ ከከፍተኛ ሊጉ በዝቅተኛ ነጥብ ሲወርድ አማኑኤል በተቃራኒው ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ መርቷል፡፡ ” አዎ በመቐለ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፌያለው፡፡ በዳሽን የመሰለፍ እድል አላገኘውም ፤ በሰሜን ሸዋ ደግሞ በጥቂት ጨዋታዎች ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡ ሆኖም በሰሜንሸዋ በተጫወትኩባቸው ጨዋታዎች ላይ የተመለከቱኝ መቐለ ከተማዎች ወደዚህ አምጥተውኝ ጥሩ የውድድር አመት አሳልፌያለሁ፡፡ ”
በዘንድሮው አቋሙ የበርካቶችን ቀልብ የሳበውና በመጪዎቹ አመታት ያንጸባርቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ አጥቂዎች መካከል የሆነው አማኑኤል በርካታ ህልሞች እንዳሉት ይናገራል “በትልቅ ደረጃ ማሳደግ እፈልጋለው፡፡ እንደማንኛውም ተጫዋች ራሴን አሳድጌ ለታላላቅ ክለቦች እና ለብሔራዊ ቡድን የመጫወት ህልም አለኝ፡፡ ”
በመጨረሻም አማኑኤል በበርካታ ክለቦች አይን ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ስሙ ከተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር እየተያያዘ ይገኛል፡፡ ሆኖም አጥቂው የቀጣይ አመት ማረፊያውን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ ” እሱን ወደፊት ብናየው ይሻላል፡፡ ” የሚል አጭር መልስ ሰጥቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *