​የካፍ ለውጦች ለኢትዮጵያ ምን ይዘው ይመጣሉ?

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአፍሪካ ዋንጫ፣ በክለብ ውድድሮች እና የወጣቶች ውድድር ላይ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ ውሳኔ የተሰጠባቸው አዲሶቹ አሰራሮች አስተያየት ሰጪዎችን ለሁለት የከፈሉ ሲሆን በዚህ ጽሁፍ ውሳኔዎቹ ለኢትዮጵያ ምን ይዞ ይመጣል የሚለውን እንመለከታለን፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ

የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ በ24 ሃገራት መካከል ይካሄዳል፡፡ ይህ ውሳኔ በአፍሪካ ካሉት ጥራት ያላቸው ብሔራዊ ቡድኖች እጥረት አንጻር የውድድሩን ጥራት የሚገድል እንደሆነ ብዙዎች ይከራከሩበታል፡፡ በቀላሉ ከማጣርያ የማለፍን እድል የሚፈጥር በመሆኑም አጓጊ የማጣርያ ጨዋታዎችን ዋጋ ቢስ እንደሚያደርጋቸው እርግጥ ነው፡፡

በሌላ ጎኑ ደግሞ የተሳታፊ ቁጥሩ መጨመር ለውድድሩ ባይተዋር ሆነው የቆዩ ፣ ከአመታት አንድ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ቡድኖችን ተስፋ ያለመለመ ውሳኔ ሆኗል፡፡ ለአብነትም የምድብ ማጣርያን አልፋ ወደ አፍሪካ ዋንጫ አምርታ የማታውቀው ኢትዮጵያ በውሳኔው ተጠቃሚ ሊሆኑ ከሚችሉ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በጥቂት አጋጣሚዎች የምድብ ማጣርያዋን በሁለተኝነት ማጠናቀቅ የቻለችው ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በሚደረጉ የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በመደበኝነት ለመካፈል ከዚህ ቀደም ከነበረው ያነሰ ፈተና የሚገጥማት ቢሆንም የብሔራዊ ቡድን የጥንካሬ ደረጃዋን ማሻሻል ይጠበቅባታል፡፡

በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማርጣያ በምድብ 6 የተደለደለችው ኢትዮጵያ በጋና 5-0 ተሸንፋ የምድቡ ግርጌ ላይ የምትገኝ ሲሆን ቢያንስ በሁለተኝነት ከሚያልፉ ሀገራት መካከል ሆና አፍሪካ ዋንጫውን ለመቀላቀል ከሴራሊዮን እና ኬንያ ነጥቦች መሰብሰብ ይጠበቅባታል፡፡

ከላይ ቻርቱ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ለመካፈል ከበቃችባቸው ውድድሮች መካከል በአዘጋጅነቷ (3) ፣ ያለፈው ውድድር ቻምፒዮን በመሆኗ (1) ማጣርያ ባለመኖሩ (2) በአጠቃላይ 6 ጊዜ ካለ ማጣርያ ነው ያለፈችው፡፡ በ1966 በኬንያ ብትሸነፍም ኬንያ ከውድድሩ ራሷን በማግለሏ ወደ ውድድሩ አምርታለች፡፡ በ1970 (ሱዳን) ፣ በ1983 (ሊቢያ) እና በ2013 (ደቡብ አፍሪካ) በተስተናገዱት ጨዋታዎች ደግሞ በጥሎ ማለፍ መልክ ቢበዛ ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ብቻ አድርጋ ወደ አፍሪካ ዋንጫ አልፋለች፡፡ ከ1992 የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የምድብ ማጣርያ ኢትዮጵያ በ10 አጋጣሚዎች የምድብ ማጣርያ ብትቀላቀልም በአንዳቸውም ወደ አፍሪካ ዋንጫው መግባት አለመቻሏን ስንመለከት የተሳታፊዎች ቁጥርን ወደ 24 የማሳደጉ ውሳኔ ለኢትዮጵያ መልካም ነገር ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከ8 ወደ 16 ክለቦች በተቀየረው የአፍሪካ የክለቦች የምድብ ውድድር አሰራር ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ምድብ ድልድሉ እንዲገባ እንደረዳው ሁሉ የአፍሪካ እግርኳስ ላይ በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ ሀገራት ጋር የሚደለደሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በሁለተኝነት ወደ አፍሪካ ዋንጫው የመሻገር እድላቸው ይሰፋል፡፡

ከተስፋ ባሻገር…

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በተለይም በፌዴሬሽኑ አመራር እና በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ላይ የተቀመጡ አሰልጣኞች ካለ ብዙ ጥረት የሚገኙ ድሎችን እንደትልቅ ስኬት የመቁጠር ባህል ይታያል፡፡ የሴካፋ ውድድሮችን ማሸነፍ ፣ የቻን ውድድር ላይ መካፈል እና አንድ ወይም በሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ብቻ ለአፍሪካ ዋንጫው መካፈል እንደ ግዙፍ ስኬት ተጋንኖ በሚወራባት ሀገር በቀጣይ አፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በቀላል ፈተና መካፈል መቻል እንደ እድገት መለኪያ በመቁጠር ወደተሳሳተ መንገድ እንዳይመራን ያሰጋል፡፡

ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆነን በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት የደርሶ መልስ ተጋጣሚዎችን ብቻ አልፈን ወደ አፍሪካ ዋንጫው መግባታችን የእግርኳሳችን እድገት ነጸብራቅ ሆኖ መታየቱና ራሳችንን ከታላላቅ የአፍሪካ እግርኳስ ሀገራት ተርታ ያሰለፍን ያህል ተሰምቶን ነበር፡፡ ነገር ግን እግርኳሳችን ከደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ የወረደበት ቁልቁለት ሁላችንም የተመለከትነው ነው፡፡

የተዘበራረቀ ካሌንደር ለማስተካከል በር የሚከፍተው የውድድር ወቅቶች ለውጥ

የአፍሪካ ዋንጫው የሚካሄድበት ወቅት ከጥር ወር ወደ ሰኔ/ሐምሌ የተዛወረ ሲሆን የክለቦች ውድድር (ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) መጀመርያ ወቅት ከጥር (ጃንወሪ) ወደ ኦገስት (ነሀሴ) ተሸጋግሯል፡፡

ይህ ለውጥ ከአውሮፓውያን የውድድር ዘመን ፎርማት ጋር ተመሳሳይ በሆነ አካሄድ ለምትጠቀመው ኢትዮጵያ መልካም ነገሮችን ይዞ ሊመጣ የሚችል ነው፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ 24 መለጠጡን ተከትሎ ከሌላው ጊዜ በተሻለ የማለፍ እድል የሚሰጣት ኢትዮጵያ ወደ ውድድሩ የምታልፍ ከሆነ በአዲሱ አሰራር የአፍሪካ ዋንጫ ጁን (ሰኔ) ላይ የሊግ ውድድሯን ካጠናቀቀች በኋላ ለማካሄድ ያግዛታል፡፡

በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ መሳተፏን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር ሳይጠናቀቅ ተጫዋቾች ወደ አፍሪካ ዋንጫው በመጓዛቸው ውድድሩ ምንያህል ተዘበራርቆ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ የጥሎ ማለፉ ውድድር እንኳን የተጠናቀቀው በቀጣዩ አመት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ለውጥ ሊጉን ወጥ በሆነ የውድደር ወቅቶች ለማስኬድ እንዲያስገድደን በር ይከፍታል፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ ዋንጫው ወደ ሰኔ ወር በመዛወሩ ሊጋችንን ቢያንስ ግንቦት ወር ላይ እንዲጠናቀቅ የሚያደርግ አሰራር እንድንከተል ያደርገናል፡፡

የአፍሪካ የክለቦች ውድድሮች ከኢትዮጵያ ጋር በሚመሳሰል የውድድር ወቅት እንዲካሄድ መወሰኑ የሀገራችንን እግርኳስ ጊዜ አጠቃቀም እንዲስተካከል የሚያስገድድ በመሆኑ በመልካም ጎኑ የሚነሳ ነው፡፡

ከላይ በሰንጠረዡ እንደሚታየው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመናት የሚጀመርባቸው እና የሚጠናቀቅባቸው ወቅቶች ወጥ ያልሆኑ ናቸው፡፡ የአፍሪካ የክለብ ውድድሮች በኦገስት (ነሐሴ አጋማሽ) የሚጀምሩ በመሆኑ በውድድሩ የሚካፈሉ የኢትዮጵያ ክለቦች የግድ በነሀሴ ወር ወደ ውድድር መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ የውድድር ዘመን መጀመርያ ወቅትም ከአፍሪካ ውድድር ጋር የተቀራረበ እና አብሮ የሚሄድ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በጥቅምት እና ህዳር ወራት የሚጀመር ከሆነ ግን የውድድሩ መጠናቀቂያ ወቅት ወደ ክረምት እየገፋ ስለሚሄድ በቀጣዩ አመት የአፍሪካ ውድድር ላይ ለሚካፈሉ ክለቦች በቂ እረፍት የማይሰጥ ይሆናል፡፡

የአፍሪካ የክለቦች ውድድር ኦገስት (ነሀሴ አጋማሽ) ሲጀመር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአዲስ አመት መግቢያ ቀናት ላይ የሚጀመር ከሆነ ቢበዛ በሜይ (ግንቦት) ወር መጀመርያ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ሰኔ ፣ ሐምሌ እና ነሐሴ ወራትን በእረፍት እና በቅድመ ውድድር ዘመን አሳልፈው ወደ ውድድር እንዲገቡ ያግዛቸዋል፡፡ ይህም በአፍሪካ ውድድር አስገዳጅነት ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲጓዙ በር የሚከፍት መልካም አጋጣሚ ይሆናል፡፡

የወጣቶች እግርኳስ ውድድር ማጣርያዎች

ካፍ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የአፍሪካ ከ17፣ 20 እና 23 ዓመት በታች ውድድሮች የሚደረጉ ማጣሪያዎች ልክ እንደቻን በዞን ተከፋፍሎ ይካሄዳል፡፡ ይህም እንደዋናው የአፍሪካ ዋንጫ ሁሉ በማጣርያ ወደ ውድድሩ ማለፍ ዳገት ለሆነባት ኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ እንደ ባህል የተለመደው ነገር ስለ ወጣቶች ትኩረት የሚሰጠው የወጣቶች ውድድሮች በሚኖሩበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በማጣርያው የወጣቶች እግርኳስ ላይ በተደጋጋሚ የበላይነታቸውን ባስመሰከሩ የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ተሸንፋ በጊዜ የምትሰናበት በመሆኑ ወጣት ተጫዋቾቻችን በውድድሩ ላይ የመታየት ተስፋቸው የመነመነ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአዲሱ አሰራር በዞኗ ማጣርያዋን የምታደርገው ኢትዮጵያ የተሻለ የማለፍ እድል የምታገኝ በመሆኑ ለወጣት/ታዳጊ ቡድኖቻችን በተደጋጋሚ በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ልምድ የማካበት አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡

በሰንጠረዡ ላይ እንደሚታየው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣት ውድድሮች ላይ የመካፈል ልምድ የላትም፡፡ ከ17 አመት ውድድር ላይ ከተካፈለች 14 አመታት ሲቆጠሩ ከ20 አመት በታች ውድድር ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው በ2001 (እኤአ) ራሷ ባስተናገደችበች ውድድር ላይ ነው፡፡ በመሆኑም አዲሱ የማጣርያ ስርአት ለኢትዮጵያ ነገሮችን ቀላል ሊያደርግላትና ለአፍሪካ ውድድሮች ልትበቃ ትችላለች፡፡

ምናልባትም ማጣርያዎች በዞን የተከፈሉ መሆናቸው ለደካማው የምስራቅ አፍሪካ ዞን የሚሰጠው ኮታ ጥቂት ከሆነ ጠንካራ ፉክክር የሚጠብቃት ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *