አቶ አበበ ገላጋይ ለአሸናፊ በቀለ ቅሬታ ምላሽ ሰጥተዋል

ከኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተያይዞ ሰሞኑን በተፈጠረው ጉዳይ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቅሬታ የቀረበባቸው የቡድን መሪው አቶ አበበ ገላጋይ ለሶከር ኢትዮዽያ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

በቻን የመጨረሻ የማጣርያ ከሱዳን ጋር ላለበት ወሳኝ ጨዋታ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን ማድረግ ከጀመረ ቀናቶች የተቆጠሩ ሲሆን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ተያይዞ አሰልጣኝ አሸናፊ መልቀቂያ ማስገባታቸው ፣ በግል ገንዘባቸው ለቡድኑ ትጥቅ መግዛታቸው እና በተጫዋቾች ምርጫ ዙርያ የስራ ጣልቃ ገብነት መኖሩን በመግለጽ አሰልጣኝ አሸናፊ ቅሬታ ውስጥ የገቡ መሆናቸውና ከጉዳዩ ጋር ስማቸው በቀጥታ የተነሳው የቡድን መሪው አቶ አበበ ገላጋይ በጉዳዩ ላይ ለሶከር ኢትዮዽያ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እኛም እንዲህ አድርገን አቅርበነዋል ።

ከአሰልጣኝ አሸናፊ ጋር ስላላቸው ግኑኝነት

” ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር ጤናማ የሚባል ግኑኝነት ነው ያለን፡፡ በስራም ላይ በጥሩ ሁኔታ በመግባባት እየሰራን ነው፡፡ አሰልጣኙ ለሚያስፈልጋቸው ነገሮች እና ለሚያቀርቡት ጥያቄ ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው አድርጌያለሁ፡፡ ”

አሰልጣኙ ጥሪ ያደረጉላቸው ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ እንዳይቀላቅሉ አድርገዋል ስለመባሉ

” በፍፁም ከእውነት የራቀ መሰረተ ቢስ ወሬ ነው፡፡ እኔ በምንም መንገድ ተጫዋች ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንዳይቀላቀሉ አላደረግኩም፡፡ እንዲያውም መታወቅ ያለበት ቁም ነገር ከጋና ጨዋታ በፊት አሰልጣኙ አስቻለው ታመነ እና ሳላዲን በርጌቾን ያልመረጡ ቢሆንም እኔ ባደረኩት ጥረት እንዲካተቱ አድርጌያለሁ፡፡ ከአሰልጣኙ ጋር በመነጋገር እና በመግባባት ተጫዋቾቹ ለብሔራዊ ቡድኑ እንደሚያስፈልጉ ገልጬ በተለይ አሰልጣኝ አሸናፊ ፣ አስቻለው ታመነ እና እኔ ባለሁበት በካፒታል ሆቴል ባደረግነው ውይይት አስቻለው ታመነ ያልተመረጠበትን ምክንያት ፤ በጥሩ መንፈስ በእሱ ከፍተኛ እምነት እንዳለው በመግለፅ ” ያልመረጥኩህ ድካም አለብህ ብዬ ነው፡፡ አሁን ግን ስታስፈልገኝ ነው የመረጥኩህ” በማለት በመግባባት እንዲጠራ መደረጉ መታወቅ አለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ከጅቡቲ ከመመለሳችን በፊት ስድስቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች ሆቴል በመግባት ለመልሱ ጨዋታ እንዲጠብቁን አሰልጣኙ በጠየቁት ጥያቄ መሰረት እንዲገቡ ቢደረግም ሳላዲን ሰኢድ ፤ ሳላዲን በርጌቾ እና ናትናኤል ዘለቀ ሀገር ውስጥ ባለመኖራቸው ምክንያት ሆቴል ያልገቡ በመሆናቸው ሳይካተቱ ቀሩ እንጂ እኔ ያስቀረሁት ተጨዋች የለም ። በአሁን ሰአት ከበኃይሉ አሰፋ በቀር ምንተስኖት አዳነ ፣ አስቻለው ታመነ ተቀላቅለው ከቡድኑ ጋር እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ በጣም መታወቅ አለበት፡፡ ”

በአሰልጣኝ ስራ ውስጥ ጣልቃ ገብነት አለ ስለለተባለው ጉዳይ

” አሰልጣኙ የሚሰራውን ስራ የመከታተል እና የመገምገም ኃላፊነት ፌዴሬሽኑ አለበት፡፡ አንድ የቡድን መሪ የሚመረጠው የእግር ኳስ እውቀቱ ልምዱ ፣ ከአስተዳደር ጋር ባለው ቅርበት ታይቶ ነው፡፡ እስከ ዛሬም በጥሩ መግባባት ምን ይደረግ ምን ይጨመር በማለት አብረን እንደሰራን ነው የማቀው፡፡ ሆኖም አንዳንድ ግለሰቦች በግል ጥላቻ ተነሳስተው ያስወሩት ወሬ ነው፡፡ ”

አሰልጣኙ መልቀቂያ ስለ ማስገባታቸው

” ስለዚህ ጉዳይ ምንም አላውቅም፡፡ ”

በዚህ ጉዳይ ላይ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ያላቸውን ሀሳብ እንዲሰጡ ጠይቀን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በዚህ ፁሑፍ ማካተት ያልቻልን ሲሆን የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ዛሬ ወደ አዳማ በማቅናት ከቡድኑ አባላት ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *