በመጪው እሁድ ከኬንያ አቻው ጋር ለቻን ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ በናይሮቢ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሀዋሳ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ሀዋሳ ያቀኑ ዋልያዎቹ ሳውዝ ስታር ሆቴል የተቀመጡ ሲሆን ትላንት ብቻ(ሰኞ) በቀን 2 ጊዜ ልምምድ አድርገዋል፡፡ የግንባታው 2/3 ኛ ላይ የደረሰው አዲሱ የሀዋሳ ስታድየምም የልምምድ ፕሮግራሙ እየተካሄደበት ይገኛል፡፡
በቡድኑ ውስጥ 2 አዳዲስ ተጨዋቾች የተካተቱ ሲሆን የንግድ ባንኩ ታዳጊ ቢንያም በላይ እና የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ምህረትአብ ገ/ህይወት 24ቱን ተጨዋቾች የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና ረዳቶቻቸው ጠንካራ የአካል ብቃት እና የታክቲክ ስራዎችን በማስራት እንዲሁም እርስ በእርስ ጨዋታዎችን በማጫወት የመልሱን ጨዋታ በብቃት ለመወጣት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑ ዛሬ የሀዋሳ የመጨረሻ ዝግጅቱን 10፡00 ካካሄደ በኋላ ነገ ወደ አዲስ አበባ አምርቶ አርብ ወደ ኬንያ ይጓዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡