የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና 8ኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የምድብ ጨዋታ እሁድ ሲጠናቀቅ ወደ 2ኛ ዙር ያለፉ ክለቦች ሙሉ ለሙሉ ታውቀዋል፡፡

ምድብ 1

በ8:00 በሙሐመድ ሁሴን አሊ አል–አሙዲ ስታድየም በሽረ እንዳስላሴ ቢ እና ኢተያ ከተማ ጨዋታ በተደረገው ጨዋታ ሽረ 1-0 በማሸነፍ ወደ 2ኛ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በፈጣን እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ በ3ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተላከውን ኳስ አምበሉ ሸሻይ ኪዳነ አስቆጥሮ ሽረን መሪ አድርጓል።

የጨዋታው ድባብ ቀስ በቀስ አላስፈላጊ መጎሻሸሞች እና ኃይል የቀላቀለበት ጨዋታ ይዘት  እየያዘ የመጣ ሆኗል። የሽረ የአሰልጣኞች ስታፍ እና ቡድን መሪ በተደጋጋሚ ከዳኞች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ሲገቡ የተስተዋለ ሲሆን በ28ኛው ደቂቃ የሽረ ቡድን መሪ ኤፍሬም ሐዱሽ በእለቱ የመሀል ዳኛ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል።


ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እና ፈጣን የሚባል እንቅስቃሴ የተስተዋለ ሲሆን ኢተያ የሙከራ የበላይነት ወስደዋል፡፡ በ70ኛው ደቂቃ ጣሒር ሰይፍ ከሽረ ግብ ጠባቂ የተመለሰውን ኳስ አግኝቶ በጎሉ በላይ የላከው እና በ76ኛው ደቂቃ ሁለት የሽረ ተከላካዮች አታሎ በተመሳሳይ በጎሉ አናት የላከው ኳስ በኢተያ በኩል ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ። በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ባይደጋግምም መጎሻሸሞች የተስተዋሉ ሲሆን በ90ኛው ደቂቃ የኢተያው አህመድ ሁሴን በሽሬ ግብ ጠባቂ ላይ በፈፀመው ጥፋትት የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል። ጨዋታውም በሽረ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ሰአት በተካሄደ ሌላ ጨዋታ ያሶ ከተማ ሾኔን 3-1 ቢያሸንፍም ተያይዘው ከምድባቸው ተሰናብተዋል፡፡

ምድብ 2
ከዚህ ምድብ ድሬዳዋ ኮተን ከምድቡ አስቀድሞ ማለፉን በማረጋገጡ ሌላኛውን አላፊ ቡድን የሚለዩ ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ መልካ ቆሌ ላይ መርካቶ አካባቢ ቤንችማጂ ፖሊሰን 2-0 በመርታት ወደ 2ኛው ዙር ሲያልፍ ቡሬ ከተማ ከመተከል ፖሊስ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀው ተያይዘው ከምድቡ ተሰናባች ሆነዋል፡፡

ወደ 2ኛዙር ያለፉ ክለቦች

ምድብ 1 – የጁ ፍሬ ወልዲያ ፣ ሽረ እንዳስላሴ ቢ
ምድብ 2 – ድሬዳዋ ኮተን ፣ መርካቶ አካባቢ
ምድብ 3 – ናኖ ሁርቡ ፣ አሳሳ ከተማ
ምድብ 4 – ሰንዳፋ በኬ ፣ ነስር ክለብ
ምድብ 5 – መርሳ ከተማ ፣ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ
ምድብ 6 – አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፣ ገንደውሀ ከተማ
ምድብ 7 – ጉለሌ ክፍለከተማ ፣ ገንፈል ውቅሮ
ምድብ 8 – ሺንሺቾ ከተማ ፣ ጫንጮ ከተማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *