አህመድ አህመድ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን በይፋ ጀምረዋል

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ፕሬዝደንት ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን ዛሬ አዲስ አበባ ላይ ጀምረዋል፡፡ አህመድ እሁድ አመሻሽ የቡርኪናፋሶ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ የደረሱ ሲሆን ሰኞ ጠዋት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታን እና የካፍ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅትም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ርዕስቱ ይርዳው እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁኒይዲ በሻ እና የጅቡቲ እግርኳር ፌድሬሽን ፕሬዝደንት እና የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሱሌማን ሃሰን ዋቤሪ ተገኝተዋል፡፡


ፕሬዝደንት አህመድ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚን የጎበኙ ሲሆን በአካዳሚው የሚገኙ ማዕከሎች የሚሰጡትን አገልግሎት ላይ መግለጫ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት በማዕከሉ ሜዳ በስልጠና ላይ የተገኙት የአሴጋ አካዳሚ ታዳጊዎች ከፕሬዝደንቱ ጋር የመተዋወቅ እድልን አግንኝተዋል፡፡ አሴጋ አካዳሚ ከወራት በፊት በድንገት ከዚህ አለም በሞት ያጣናው የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን አጥቂ አሰግድ ተስፋዬ ስር ይተዳደር የነበረ አካዳሚ ነው፡፡

የ57 ዓመቱ ማዳጋስካራዊ በመቀጠል በአዲስ አበባ እየተገነባ በሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም በመገኘት የግንባታውን ሂደት የተመለከቱ ሲሆን ግንባታውን ከሚያከናውነው የቻይና ኩባንያም ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ አህመድ አህመድ በቀኑ የመጨረሻ መርሃ ግብርም አያት አከባቢ ያለፉትን 14 አመታት ተገንብቶ መጠናቀቅ ያልቻለውን የካፍ ማዕከል ጎብኝተዋል፡፡ ፕሬዝደንት አህመድ ዛሬ 9 ሰዓት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማሪያም ደሳላኝ ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *