ቢኒያም በላይ ለአልባኒያ ክለብ ፈርሟል

ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ በጀርመን እና ኦስትሪያ ያሳለፈውን ያልተሳካ ሙከራ በኃላ ወደ አልባኒያ አምርቶ ከሃገሪቱ ሃያል ክለቦች ተርታ ለሚመደበው ኬኤፍ ሴኬንደርብዩ ኮርሲ ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል፡፡ ቢኒያም ለደቡብ ምስራቅ የአልባኒያው ክለብ ለመጫወት የሶስት ዓመት ውል ፈርሟል፡፡ ሆኖም ክለቡ ስለቢኒያም ዝውውር መረጋገጫ እስካሁን አልሰጠም፡፡

ተጫዋቹ ወደ ጀርመን አቅንቶ የሙከራ ግዜ እንዲያሳልፍ የረዱት ጀርመናዊው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የቴክኒክ አማካሪ ዩአኪም ፊከርት ቢኒያም በአልባኒያው ክለብ ውል መፈረሙን ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡ “አሁን ባለኝ መረጃ መሰረት ቢኒያም በአልባኒያው ክለብ ሴኬንደርብዩ ኬርሲ የሶስት አመት ውል ፈርሟል፡፡ ክለቡ ጥሩ ብቃት ያላቸውን አፍሪካዊያን ተጫዋቾችን በማስፈረም የሚታወቅ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ አራት ግዜ የአልባኒያ ሊግ ማሸነፍ የቻለ ጠንካራ ክለብ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይ ቢኒያም በጀርመን በዳይናሞ ድረስደን እና አዜንበርገር አወ እንዲሁም በኦስትሪያ የሬድ ቡል ሳልዝበርግ መጋቢ ክለብ በሆነው ኤፍሲ ላይፈሪንግ የሙከራ ግዜ ካሳላፈ በኃላ ወደ አልባኒያ አቅንቷል፡፡ በአልባኒያም ከሃገር ውጪ የመጫወት ህልሙን ቢኒያም ማሳካት ችሏል፡፡

1925 እ.ኤ.አ. የተመሰረተው ሴኬንደርብዩ በኮርሲ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኝ ክለብ ነው፡፡ 12000 ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው የሴኬንደርብዩ ስታዲየም ጨዋታዎቹን የሚያደርገው ክለቡ የሰባት ግዜ የአልባኒያ ሱፐርሊጋ ቻምፒዮን ነው፡፡ በ1933 ያሳካውን የሊግ ድ ለመድገምም 78 ዓመታትን መታገስ ግድ ብሏቸዋል፡፡ ክለቡ ከ2010/11 የውድድር ዘመን ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት አመታት የአልባኒያ ሱፐርሊጋ ቻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በ72 ነጥብ 3ተኛ ደረጃን በማግኘት ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ክለቡ በዮሮፓ ሊግ የምድብ ውስጥ እንዲሁም በቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ለመግባት የመጨረሻ የማጣሪያ ዙር መድረስ የቻለ የመጀመሪያው የአልባኒያ ክለብ ነው፡፡

አዲሱ የአልባኒያ ሱፐርሊጋ የውድድር ዘመን በመስከረም ወር ሲጀመር ሴኬንደርብዩ ኮርሲ ፍላሙርታሪን በሜዳው ያስተናግዳል፡፡ ወደ ዩሮፓ ሊግ ምድብ ውስጥ ለመግባትም የክሮሺያው ሃያል ዳይናሞ ዛግሬብ ጋር ተፋጧል፡፡ ሴኬንደርብዩ በሶስተኛ ዙር ማጣሪያ የፍቅሩ ተፈራ የቀድሞ ክለብ የሆነውን የቼክ ሪፐብሊኩን ማልዳ ቦልስላቭን በመለያ ምቶች 4-2 አሸንፎ ነው፡፡

ቢኒያም ወደ አልባኒያ ያደረውን ዝውውር ተከትሎ በሃገሪቱ የሚጫወት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ይሆናል፡፡ ልክእንደቢኒያም ሁሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አማካይ ጋቶች ፓኖም ወደ ሩሲያው አንዚ ማካቻካላ በሶስት ዓመት ውል ማምራቱ የሚታወስ ሲሆን አዳማ ከተማው ተከላካይ ሙጂብ ቃሲም በሞሮኮው ኢትሃድ ታንገ የሙከራ ግዜ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *