የሰኔ 26 አጫጭር ዜናዎች

-የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ግማሽ ፍፃሜ እና ፍፃሜ ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ አመት ተዘዋውረዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ የክለቦች የበጀት አመት ሰኔ 30 በመጠናቀቁ ጨዋታዎችን ማከናወን እንዳልቻለ ተነግሯል፡፡ የዘንድሮው ውድድር በህዳር ወር ቢጀመርም የጨዋታዎች ቀን በተደጋጋሚ ተቀይረዋል፡፡ በግንቦት ወር ሊካሄዱ የነበሩት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ወደ ሰኔ ፤ ሰኔ 23 ሊካሄዱ የነበሩት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋዎች ወደ ሐምሌ 2 አሁን ደግሞ ወደ ቀጣዩ አመት ተዘዋውረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በ2005 መጠናቀቅ የነበረበት ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ ወደ 2006 መተላለፉ አይዘነጋም፡፡

– የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን ማጣርያ ከኬንያ ብሀሄራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የኮሞሮስ ዳኞች ይመሩታል፡፡ ዋና ዳኛው አሊ ሞሃመድ አዴላይድ ሲሆኑ ረዳቶቹ ሱሌይማን አማላዲኔ እና ሀማዲ ሁሴን ናቸው፡፡ የጨዋታው ኮሚሽነር ደግሞ ሩዋንዳዊው ካይጁካ ጎስፓርድ ናቸው፡፡

– የነገውን ጨዋታ የደቡብ አፍሪካው ሱፐር ስፖርት 9 ኢስት እና የኬንያው ስታር ታይምስ ስፖርት ፣ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ደግሞ በሬድዮ በቀጥታ ያስተላልፉታል፡፡

– የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኬንያ መልካም መስተንግዶ እንዳልገጠመው ተነግሯል፡፡ የህዝብ ግንኙነቱ አቶ ወንድምኩን አላዩ ዛሬ ጠዋት ከብስራት ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለቡድኑ የተመደበለት መኪና ከደረጃ በታች እንደነበርና ልምምዳቸውን ያከናወኑት በካሜራ መብራቶች ታግዘው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና የቡድን መሪው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ረቡእ እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኬንያዎች ችግር ሊፈጥሩባቸው እንደሚችሉና ለዚህም በአእምሮው ረገድ እንደተዘጋጁ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡

– በሴካፋ ካጋሜ ካፕ ላይ የሚሳተፈው አዳማ ከነማ ጨዋታዎቹን የሚያደርግባቸው ቀናት ታውቀዋል፡፡ ከጁላይ 18 እስከ ኦገስ 2 በታንዛንያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም በሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ውድድር የኢትዮጵያው አዳማ ከነማ በምድብ 3 ከታንዛንያው አዛም ፣ ከዩጋንዳው ካምፓላ ካፒታል ሲቲ አውቶሪቲ እና ከደቡብ ሱዳኑ ማላኪያ ጁባ ጋር የሚፋለም ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታውን ጁላይ 19 (ከ15 ቀን በኋላ) ከማላኪያ ጁባ ጋር በብሄራዊ ስታድየም ያደርጋል፡፡ ከ3 ቀናት በኋላ ደግሞ ከካምፓላ ሲ.ሲ.ኤ. ጋር የምድቡን 2ኛ ጨዋታ በካሪን ስታድየም ያደርጋል፡፡ የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ከአዛም ጋር ጁላይ 25 በብሄራዊ ስታድየም ያደርጋል፡፡

ውድድሩ የምስራቅ አፍሪካ የእግርኳስ ውድድሮች በሚተላለፉበት ሱፐር ስፖርት 9 ኢስት ላይ በቀጥታ ይተላለፋል፡፡

– የሴቶች ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ፍፃሜ በደደቢት እና አርባምንጭ ከነማ መካከል ማክሰኞ ይካሄዳል ( ምንጭ – ኑራ ኢማም)

– ከ17 አመት በታች ጥሎ ማለፍ በአዲስ አበባ ስታድየም መካሄድ ጀምሯል፡፡ ዛሬ 8፡00 በተካሄደ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አበባ ከተማን 2-0 አሸንፏል፡፡ ቀጥሎ በተካሄደው ጨዋታ ደግሞ ሀረር ሲቲ ኤሌክትሪክን 1-0 እየመራ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ (ኑራ ኢማም)

ምስል — ብሄራዊ ቡድኑ በኬንያ የተደረገለትን አቀባበል የሚያሳዩ ምስሎች (ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተላኩ)

CAM03451 CAM03456 CAM03462