ኢትዮጵያ ቡና ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ድራጎን ፖፓዲችን አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ ታውቋል፡፡ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በ2 አሰልጣኞች ያገባደደው ኢትዮጵያ ቡና በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የውጪ ዜግነት ያለውን አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡
ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የህዝብ ግንኙነት ባገኘነው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ቡና ከሰርቢያዊው የ69 አመት አሰልጣኝ ጋር ውጤቱ ታይቶ ወደፊት የሚታደስ የ1 አመት ኮንትራት የተፈራረመ ሲሆን በጥቅማ ጥቅም እና ሌሎች ጉዳዮች ላይም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በአሰልጣኙ ይፋዊ ቅጥር ጉዳይ ላይ ጥልቅ ማብራርያ ረቡእ በሚኖረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደሚሰጡም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና በቅርቡ የቴክኒክ ዳይሬክተር አደርጎ የሾማቸው አቶ ደሳለኝ ዛሬ በክለቡ የሬድዮ ፕሮግራም ላይ በአዲሱ አሰልጣኝ ቅጥር ዙርያ በሰጡት አስተያየት ከአሰልጣኙ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ተናግረዋል፡፡
‹‹ ከብዙ ክለቦች ጋር ሰርቷል፡፡ የበርካታ አመታት የተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ልምድም አለው፡፡ እኔ የአሰልጣንነት ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት በቅርቡ ነው፡፡ ሁለታችንም በሙያው ውስጥ ስላለን ከፖፓዲች ጋር ተግባብተን መስራት እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ፍልስፍና መጥፋት የለበትም፡፡ የክለቡ የአጨዋወት ስታይል እንዳለ ሆኖ የተጫዋችን የብቃት ደረጃ ማሻሻል አለብን፡፡ ደጋፊው የሚፈልገውን ማራኪ አጨዋወት ከውጤት ጋር ማጣመር ይጠበቅብናል፡፡ ››
‹‹ ለውጤታማነት ጠንካራ ስራ እና ትእግስት ያስፈልጋል፡፡ ያሉት ተጫዋቾች ሙሉ ብቃታቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ መስራት እንደሚገባንና ለቡድኑ በሚያስፈልጉት ተጫዋቾች ዙርያ ከአሰልጣኙ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ››
ፌብሩወሪ 14 ቀን 1946 በሰርቢያ መዲና ቤልግሬድ የተወለዱት የ69 አመቱ ፖፓዲች ከ1968 እስከ 1977 በቆየው የተጫዋችነት ዘመናቸው ለከተማቸው ክለብ አር.ኤ.ዲ ቤልግሬድ እና ኦአፍኬ ቤልግሬድ ፣ ኦሎምፒያ ፣ ሀርለም እና የቤልጅየሙ ሊርስ ክለብ ተጫውተው አሳልፈዋል፡፡
ፖፓዲች በአሰልጣኝነት ዘመናቸው በሰርቢያ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከመስራታቸው በተጨማሪ በአፍሪካ እግርኳስ የካበተ ልምድ እና ውጤት አላቸው፡፡ በዩጋንዳ ከኤክስፕረስ ካምፓላ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሱ ሲሆን ፣ ከታንዛኒያው ታላቅ ክለብ ሲንባ ጋር ደግሞ የሊጉን እና የሴካፋ ክለቦች ሻምፒዮናን አንስተዋል፡፡ በአንጎላው ፔትሮ አትሌቲኮ ሉዋንዳ ክለብ የሀገሪቱን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ናሽናል ካፕ አንጎላን አሸንፈዋል፡፡ በጋና የሃገሪቱን ትልቅ ክለብ ኸርትስ ኦፍ ኦክ እና ኪንግ ፈይሰል ክለቦችን አሰልጥነዋል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ በሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ሰርተዋል፡፡