ኢትዮጵያ በበርካታ ደጋፊ ታጅባ ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር አለፈች (የጨዋታ ሪፖርት)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሀገር ውስጥ ሊጎች በሚጫወቱ ተጫዋቾች በሚዋቀረው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ 180 ደቂቃ ብቻ ቀርቶታል፡፡ ዋልያዎቹ ዛሬ በናይሮቢ ባደረጉት ጨዋታ 0-0 ተለያይተው በድምር የ2-0 ውጤት ወደ ተከታዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ጨዋታው በኬንያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ድጋፍ የታጀበ ሲሆን በአንፃሩ ጥቂት ኬንያውያን ብቻ ስታድየም በመታደማቸው የኒያይዎ ስታድየም አመዛኝ ክፍል ተመልካች አልባ ሆኖ ተስተውሏል፡፡

 

የመጀመርያ አጋማሽ

በጨዋታው መጀመርያ ሻካቫ በጋቶች ፓኖም ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የጨዋው የመጀመርያ የማስጠንቀቅያ ካርድ ተሰጥቶታል፡፡

በ17ኛው ደቂቃ ላይ አሊ አቦንዶ የመታውን የቅጣት ምት ታሪክ ጌትነት መልሶታል፡፡ የተመለሰውን ኳስ የኬንያ ተጫዋቾች ቢያገኙትም ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ በመገኘታቸው በመልስ ምት ጨዋታው ቀጥሏል፡፡

በ22ኛው ደቂቃ ላይ ኬንያዎች በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ቢደርሱም ሚዬኖ በግቡ አግዳሚ ወደ ውጪ ሰድዷታል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ሚካኤል ኦሉንጋ ከቅርብ ርቀት የመታው ኳስ በተመሳሳይ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

በ26ኛው ደቂቃ በዋልያዎቹ በኩል የመጀመር ልትባል የምትችል ሙከራ በኤፍፌም አሻሞ አማካኝነት ተደርጓል፡፡ ኤፍሬም ከግራ የፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ አካባቢ አክርሮ የመታትን ኳስ የኬንያው ግብ ጠባቂ ይዞበታል፡፡

በ44ኛው ደቂቃ ላይ ታሪክ ጌትነት ኳስን ይዞ በመቆየቱ ለኬንያ 2ኛ ቅጣት ምት ተሰጥቷል፡፡ አሊ አቦንዶ የመታውን ኳስም የዋልያዎቹ ግድግዳ በቀላሉ መልሶታል፡፡ ኢትዮጵያዎች የተመለሰውን ኳስ ተጠቅመው በፈጣን መልሶ ማጥቃት እጅግ ለግብ የቀረበ የግብ እድል ቢያገኙም አምበሉ በኃይሉ አሰፋ በግቡ አግዳሚ ወደ ውጪ ሰድዷታል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ መጠናቀቅያ ላይ የእለቱ ዳኛ ለራምኬ ሎክ ሳይነካ ወድቋል በሚል የማስጠንቀቅያ ካርድ አሳይተዋል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በ0-0 ውጤት ተጠናቋል፡፡

 

ሁለተኛ አጋማሽ

ከእረፍት መልስ ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ቅያሪ ስታደርግ ባዬ ገዛኸኝ ቢንያም አሰፋን ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመርያም ኢትዮጵያ በፈጣን ቅብብል ወደ ግብ ደርሳ የሞከረችው ኳስ በኬንያው ግብ ጠባቂ ቦንፋየር ኦሊች ጥረት ግብ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

በ53ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ኦሊች ወደ ውጪ አውጥቷታል፡፡

በ58ኛው ደቂቃ ጄስ ዌር በግንባሩ የገጨውን ኳስ ታሪክ ጌትነት በግቡ አግዳሚ ወደ ውጭ አውጥቷታል፡፡

በ61ኛው ደቂቃ አሊ አቦንዶ ላይ በተሰራ ጥፋት ኬንያ የፍፁም ቅጣት ምት አገኘች፡፡ አሊ አቦንዶ ራሱ የፍፁም ቅጣት ምቱን ቢመታም የግቡ ቋሚን ለትማ ተመልሳለች፡፡ በባህርዳሩ ጨዋታ ኬቪን ኪልማኒ በተመሳሳይ የፍፁም ቅጣት ምት ማምከኑ የሚታወስ ነው፡፡

በ66ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምቱን የሳተው አሊ አቦንዶ በካጎ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡

በ68ኛው ደቂቃ ኬንያዎች ኳስ በእጅ በመነካቱ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ በቅርብ ርቀት የተኘችውን የቅታት ምት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ሚካኤል ኦሉንጋ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

በ72ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ቃልቦሬ በጄስ ዌር ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ኪማኒ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡

በ76ኛው ደቂቃ ከማእዘን ምት የተገኘውን ኳስ ሚካኤል ኦሉንጋ በግንባሩ በመግጨት ለግብ የቀረበ ሙከራ ቢያደርግም አስቻለው ታመነ ከመስመር አውጥቶታል፡፡

በ79ኛው ደቂቃ ኬንያ 2ኛ የተጫዋች ቅያሪ ስታደርግ ኤሪክ ጆሃና ኬቪን ኪማኒን ቀይሮ ገብቷል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ አስቻለው ግርማ በበኃይሉ አሰፋ ተቀይሮ ገብቷል፡፡ በ89ኛው ደቂቃ ኬንያ የመጨረሻ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ኖህ ዋፉላን በኤድዊን ዋፉላ ቀይራ አስገብታለች፡፡ በ90ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያም የመጨረሻ በሆነው ቅያሪ ጋቶች ፓኖምን አስወጥታ ሙጂብ ቃሲምን አስገብታለች፡፡

መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ 5 ደቂቃ ቢጨመርም ኬንያዎች 2 የማእዘን ምት ከማግኘታቸው ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ዙር ማለፏን ተከትሎ ከቡሩንዲ ጋር ቀጣዩን የማጣርያ ጨዋታ ታከናውናለች፡፡ ቡሩንዲ በጅቡቲ ሜዳ 2-1 በማሸነፏ ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ እድሏ ሰፊ ይመስላል፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣዩን ዙር አሸንፋ ካለፈች በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በቻን ውድድር ላይ ትካፈላለች፡፡