በደደቢት እና በተጫዋቾቹ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ እልባት አግኝቷል

በደደቢት እግርኳስ ክለብ እና በ3 የቡድኑ ተጨዋቾች ዳዊት ፍቃዱ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና አክሊሉ አያናው መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፒሊን ኮሚቴ ዛሬ ውሳኔ አሳለፈ።

ከወራት በፊት የአምስት ወር ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ክለቡ ምላሽ አልሰጠንም በማለት አይናለም ኃይለ፣ አስራት መገርሳ፣ ሳምሶን ጥላሁን፣ አክሊሉ አየነው እና ዳዊት ፍቃዱ ለአስራ አምስት ቀን ያህል ልምምድ መስራት ማቋረጣቸውን ተከትሎ የደደቢት ስፖርት ክለብ አስቀድሞ የደሞዝ ክፍያው በተለያ መንገድ ተፈፅሟል ሲል ዝርዝር የክፍያ ሰነድ በማቅረብ አምስቱ ተጨዋቾች ሆን ብለው ተጨዋቾችን በማሳደም ተግርባር ውስጥ ገብተዋል በሚል የቅጣት ውሳኔ በተጨዋቾቹ ላይ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም አስራት መገርሳ ቅጣቱ ሲነሳለት ከጊዜ በኋላ አይናለም ኃይለ ይቅርታ በመጠየቁ ቅጣቱ ሲነሳለት የተቀሩት ዳዊት ፍቃዱ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና አክሊሉ አየነው የይቅርታ ደብዳቤ ቢያስገቡም ክለቡ ይቅርታቸውን ባለመቀበሉ ለኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ጉዳያቸውን ሲከታተል የቆየው የዲሲፒሊን ኮሚቴ ሰፋ ያለ የህግ ይዘቶችን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፉል፡፡

1ኛ. ደደቢት መልቀቂያ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ፌዴሬሽኑ በ3 ቀን ውስጥ መልቀቂያ እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡

2ኛ. ደደቢት በ3ቱም ተጨዋቾች ላይ ከውል መጠናቀቅ በኋላ ያስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ በመሆኑ እንዲሻር ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሰረት ቅጣቱ መነሳቱን ተከትሎ 3ቱም ተጨዋቾች ከደደቢት ክለብ ጋር ኮንትራታቸው ያለቀ በመሆኑ ወደ ሌሎች ክለቦች በቅርብ ቀናት ያመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ውሳኔውን ተከትሎ ደደቢት ስፖርት ክለብ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጠውን ምላሽ ካለ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *