ኬንያ የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫን ታዘጋጃለች

ኬንያ በህዳር 2017 የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫን እንደምታዘጋጅ ኔሽን ስፖርት የኬንያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የፌድሬሽኑ ፕሬዝደንት ኒክ ሙዌንዳም ኬንያ ውድድሩን በህዳር ወር እንደምታዘጋጅ አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጰያ በፈረንጆቹ 2015 ውድድሩን አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር እና ሀዋሳ ላይ ካስተናገደች በኃላ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫው በአዘጋጅ ሃገር እጦት ምክንያት በ2016 ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ በያዝነው አመት የሴካፋ አባል ሃገራት ሞሮኮ ላይ ባደረጉት ስብሰባ የሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫውን ጨምሮ የሴካፋ ሴቶች ቻምፒዮንሺፕ፣ ከ20 ዓመት በታች እና ከ17 ዓመት በታች ውድድሮች ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማካሄድ ምክክር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ኬንያ በ2018 የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) ማስተናገዷን ተከትሎ የሴካፋ ዋንጫውን ናኩሩ በሚገኘው አፍራ ስታዲየም እና በወደብ ከተማዋ ሞምባሳ በሚገኘው ምባራኪ ስታዲየም ለማስተናገድ እንዳቀዱ ምዌንዳ ጠቅሰዋል፡፡ የኬንያ የቻን አዘጋጅነት አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ልትነጠቅ የምትችልበት እድል መኖሩን ተከትሎ ውድድሩ ወደ ሌሎች ስታዲየሞች እና ከተሞች ሊዛወርበት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡

የሴካፋ ዋንጫውን ለማስተናገድ ፍላጎት ያሳየችው ብቸኛዋ ሃገር ኬንያ ብቻ ነች፡፡ “ሴካፋ ወደ ኬንያ እየመጣ ነው፡፡ ኬንያ ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት ያሳየች ብቸኛዋ ሃገር መሆኗን ተከትሎ እድሉ ለእኛ ተሰጥቷል፡፡ እስካሁን የተረጋገጠ ውድድሩን የምንካሄድበት ቀን ባንቆርጥም ህዳር ወር ላይ ግን ይካሄዳል፡፡” ሲሉ ምዌንዳ ለኔሽን ስፖርት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ የሴካፋ ሴቶች ቻምፒዮናን ሩዋንዳ በህዳር ወር ስታስተናግድ ቡሩንዲ የታዳጊዎች ውድድር በጥቅምት ወር እንደምታስተናግድ ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም ከውድድሮቹ አስቀድሞ ሴካፋ አዲስ አመራር በጠቅላላ ጉባኤው እንደሚመርጥ ይጠበቃል፡፡ ሴካፋን ያለፉትን ሁለት አመታት የመሩት የሱዳኑ ሙታሲም እምብዛም ስኬታማ ቆይታ አልነበራቸውም፡፡

የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የካጋሜ ክለብ ዋንጫ ከተካሄዱ ሁለት አመታት ያለፋቸው ሲሆን ከ17 ዓመት በታች እና ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች ከ2010 በኃላ ተደርገው አያውቁም፡፡
በ2015 ዩጋንዳ በሴዛር ኦኩቲ ግብ ሩዋንዳን 1-0 በመርታት የዋንጫ አሸናፊ ስትሆን ኢትዮጵያ ሱዳንን በመለያ ምት በማሸነፍ የሶስተኛ ደረጃን ማግኘቷ ይታወሳል፡፡

Photo: Nations Sport

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *