የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር አመት በአዲስ ፎርማት ይደረጋል

በ2009 የውድድር አመት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በ20 ክለቦች መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ መቆየቱ የሚታወስ ነው። ከውድድሩ መጠናቀቅ በፊትም ሆነ በኋላ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረው በተጠናቀቀው የውድድር አመት በነበረው አካሄድ ይቀጥላል ወይስ አዲስ አካሄድ የሚለው ሳይታወቅ ቀርቶ የነበረ ቢሆንም የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀጣይ አመት የውድደር አቀራረብን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መሰረት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሁለት ዲቪዚዮን የሚከፈል ይሆናል።

የኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የመጀመርያው መጠርያ ሲሆን በዚህ ምድብ ውስጥ በ2009 ውድድር ላይ በሁለቱ ምድብ ከአንድ እስከ አምስት ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ አስር ቡድኖች የሚካፈሉ ይሆናል። እነሱም ደደቢት ፣ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ፣ አዳማ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ ፣ መከላከያ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ጌዲኦ ዲላ ፣ ሲዳማ ቡና እና ድሬደዋ ከተማ ናቸው ።

ሁለተኛው ስያሜ የኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሲሆን በዚህ ዲቪዚዮን ውስጥ በ2009 ውድድር ላይ ከስድስት እስከ አስር የወጡ አስር ቡድኖች ኢትዮዽያ ቡና ፣ ቅ/ማርያም ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ፣ ቦሌ ፣ ወጣቶች አካዳሚ ፣ ጥረት ፣ አቃቂ ቃሊቲ ፣ ልደታ እና የሴቶች ክለብ ያላቋቋሙ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በቀጣይ አመት የሴቶች ቡድን ማቋቋም ከቻሉ በዚህ ዲቪዚዮን የሚካተቱ ይሆናሉ።

ከፌዴሬሽኑ ውድድር እና ስነ ስርአት ባገኘነው መረጃ መሰረት በ2011 የውድድር ዘመን በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መውጣትና መውረድ እንደሚኖር ለማረጋገጥ ችለናል።

የኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በሁለቱም ዲቪዚዮን በሚገኙ ክለቦች መካከል በሚደረግ ጨዋታ የጥሎ ማለፉ አሸናፊ የሚለይ ይሆናል።

የኢትዮዽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዲቪዚዮን ውድድር ጥቅምት 17 እንደሚጀመር ይታወቃል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *