የጀርመን ታችኛው ዲቪዚዮን ክለቦች ለእያሱ ተስፋዬ የሙከራ እድል ሰጥተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን ለደደቢት በተሰኑ ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ በመግባት የተጫወተው እያሱ ተስፋዬ ለሙከራ ወደ ጀርመን እንደሚያቀና የተጫዋቹ ወኪሎች ዴቪድ በሻ እና ስቲቨን ሄኒንግ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

የ24 አመት አማካዩ እያሱ በመጋቢት ወር የቡልጋሪያ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ክለብ የሆነውን ካሊያክራ ካቫርናን በ6 ወር ውል ቢቀላቀልም ለክለቡ እምብዛም ግልጋሎት መስጠት አልቻለም ነበር፡፡ “ክለቡ እና የክለቡ ባለቤት በእያሱ ደስተኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የስራ ፈቃድ በግዜው ባለማግኘቱ በቡልጋሪያ እንዳይጫወት አግዶታል፡፡” ይላል ሄኒንግ፡፡

እንደሄኒንግ ገለፃ ከሆነ እያሱ በጀርምን አራተኛ ዲቪዚዮን ለሚወዳደረው ቪኤፍ 06 ሂልድሸም እና በአምስተኛ ዲቪዚዮን ላይ በሚጫወተው ኤፍሲ ሜክልንበርግ ሽዌሪን የሙከራ ግዜን ያሳልፋል፡፡ በተጨማሪም አሁን ላይ ያልተረጋገጡ ሌሎች የሙከራ እድሎች በአራተኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ተጫዋቹ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡

ቪኤፍ 06 ሂልድሸም እና ኤፍሲ ሜክልንበርግ ሽዌሪን በጀርመን ዝቅተኛ ዲቪዚዮን የሚወዳደሩ ክለቦች ናቸው፡፡ ቪኤፍ 06 ሂልድሸም 2003 በቪኤፍቪ ሂልድሸም ቦሩሺያ 06 ሂልድሸም መዋህዳቸውን ተከትሎ የተመሰረተ ክለብ ሲሆን በ2015 ወደ አራተኛ ዲቪዚዮን ያደገበት ውጤቱ ለክለቡ ትልቁ ስኬት ነው፡፡ ኤፍሲ ሜክልንበርግ ሽዌሪን በ2013 የኤፍሲ ኤንትራክት ሽዌሪን እና ኤፍሲኤም ሽዌሪን ውህደት የተመሰረተ ነው፡፡

ከወር በፊት ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አማካይ ቢኒያም በላይ በጀርመን ቡንደስሊጋ 2 ለሚወዳደሩት ዳይናሞ ድረስደን እና ኤዘንበርገር አወ የሙከራ ግዜን ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *