የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ሰራተኞች ላይ በደረሰ አደጋ የሰው ህይወት ጠፍቷል

ከሁለት አመት በኃላ እንደሚጠናቀቅ የተነገረለት የአደይ አበባ ስታዲየም የግንባታ ቦታ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ከ30 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደረሰባቸው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ዘገባዎችን የሚያቀርበው አዲስ ስታንዳርድ ዛሬ ዘግቧል፡፡ የእሳት አደጋው የተነሳው በጋዝ ፍንዳታ ምክንያት ሲሆን ከአንድ ወር ያህል ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ዝምታን መምረጣቸው ተነግሯል፡፡

በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኤንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም የሰራተኞች መኖሪያ ላይ ማክሰኞ ነሃሴ 2 ከምሽቱ 2፡00 በጋዝ ፍንዳታ ምክንያት በደረሰው የእሳት አደጋ የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን ድረገፁ ዘግቧል፡፡ ከአደጋው አንድ ቀን አስቀድሞ ሰኞ ነሃሴ 7 የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ ስለስታዲየሙ ግንባታ አጠቃላይ ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን ወደ ስታዲየሙ ግን ገብተው አልጎበኙም ነበር፡፡ ከአህመድ አህመድ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከተጠናቀቀ በኃላ ነው አደጋው ሊደርስ የቻለው፡፡ እንደአዲስ ስታንዳርድ ዘገባ ከሆነ የቻይናው ኩባንያ ይሁን የመንግስት አካል በአደጋው ዙሪያ ያሉት ነገር የለም፡፡

በአደጋው ህይወታቸውን ላጡት ወገኖች ለቤተሰቦቻቸው የ15ሺህ ብር ካሳ ክፍያ ኩባንያው ለመፈፀም ቢፈልግም ተጎጂዎች ይህንን ለመቀበል እንዳልፈቀዱ ተዘግቧል፡፡ እንዲሁም አደጋ የደረሰባቸው ወገኖቻችን የህክምና እርዳታ ከኩባንያው ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡

800 ኢትዮጵያዊያን እና 200 ቻይናዊያን በስታዲየሙ ግንባታ እየሰሩ ሲገኙ የኢትጵያዊያን መኖሪያ በአማካይ 20 ሰዎች 90 ሜትር ስኩዌር በምትሆን ቦታ ሲኖሩ በአንፀሩ በቻይናዊያን ሰራተኞች መኖሪያ በአማካይ አራት ሰዎች ይገኛሉ፡፡

ከሁለት አመት በኃላ ሲጠናቀቅ 60ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም እንዳለው የተነገረለት አደይ አበባ ስታዲየም ከዚህ ቀደም የአፈር መደርመስ አጋጥሞ የሰው ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል፡፡

የፎቶ ምንጭ – አዲስ ስታንዳርድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *