ወላይታ ድቻ ተመስገን ዱባን በቋሚነት አስፈረመ

በተጠናቀቀው የውድድር አመት ሁለተኛው ዙር በውሰት አርባምንጭ ከተማን ለቆ ወደ ወላይታ ድቻ ያመራው ተመስገን ዱባ በቋሚነት ለድቻ ፈርሟል፡፡

የመስመር አጥቂው የአርባምንጭ ኮንትራቱ ዘንድሮ የተጠናቀቀ ሲሆን ያለፉትን 6 ወራት በወላይታ ድቻ ባሳለፈው የውሰት ጊዜ መልካም የሚባሉ ጊዜያት ማሳለፍ ችሏል፡፡ ይህን ተከትሎም ለአሰልጣኝ መሲይ ተፈሪ ቡድን ለቀጣዩቹ 2 አመታት ለመቆየት ተስማምቷል፡፡

በክረምቱ በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ወላይታ ድቻ ያስር ሙገርዋን ለማስፈረም ከዚህ ቀደም መስማማቱ የሚታወስ ቢሆንም ተጫዋቹ ለፋሲል ከተማ መፈረሙ ታውቋል፡፡ ክለቡም በተጫዋቹ መልቀቂያ መዘግየት እና ሌሎች መስማማት ባልቻሉባቸው ጉዳዮች ምክንያት በይፋ ሳይፈርም መቅረቱን አምኗል፡፡ ዩጋንዳዊው ኢንተርናሽናል ያስር ሙገርዋ በአሁኑ ሰአት ፋሲል ከተማን ተቀላቅሎ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ከቡድኑ ጋር እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ያስርን ያጣው ወላይታ ድቻ የአማካይ መስመር ተጫዋች ለማስፈረም በጥረት ላይ ሲሆን የቻድ ዜግነት ያለው የተከላካይ አማካይ ተጫዋች የሙከራ እድል መስጠቱ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *