ቅድመ ውድድር ዝግጅት – ፋሲል ከተማ

በመጣበት አመት በርካታ የኢትዮጵያ እግርኳስ ተከታታዮችን ባስገረመ መልኩ የሊጉ አውራ ቡድኖችን ሁሉ ሳይቀር በማሸነፍ የ2009 የውድድር አመት የፕሪምየር ሊጉ ክስተት የሚል ስያሜ የተሰጠው ፋሲል ከተማ ስፖርት ክለብ በቢሸፍቱ ከተማ በቀን ሁለት ልምምዱን በመስራት ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ፋሲል ከተማ በ2009 የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው በ30 ጨዋታ 12 አሸንፎ 7 ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በ11 ጨዋታ ተሸንፎ ፣ 32 ጎል በማስቆጠር 30 ጎሎች በማስተናገድ በ43 ነጥቦች 6ኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል ።

ከ2009 ከነበረው ስብስቡ ብዙ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ እየተዘጋጁ የሚገኙት አፄዎቹ አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡን ዋና አሰልጣኝ አድርገው ሲያስቀጥሉ የቀድሞው ዳሽን ቢራን ለተወሰኑ ሳምንታት በዋና አሰልጣኝነት ያገለገሉት አሰልጣኝ ተገኘ እንቁባይ ም/አሰልጣኝ ፣ ለሩብ ክፍለ ዘመን በኢትዮዽያ እግር ኳስ ውስጥ በተለያዩ ክለቦች በዋና አሰልጣኝነት የምናውቃቸው ሻምበል መላኩ አብርሃን ደግሞ የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር አድርጎ መርጧቸዋል።

በዘንድሮ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ በአፄዎቹ ማልያ የማንመለከታቸው ተጨዋቾች ዮሐንስ ሽኩር እና ምንተስኖት አደጎ ( ግብ ጠባቂዎች ) ፣ ያሬድ ዝናቡ ፣ ሙሉቀን ታሪኩ ፣ አቤል ያለው ፣ ታደለ ባይሳ ፣ ሰለሞን ገ/መድህን ፣ ሱሌይማን አህመድ ፣ ኤደም ኮዶዞ ናቸው።

አፄዎቹ ለዘንድሮ የውድድር አመት ተጠናክሮ ለመቅረብ በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎ ካደረጉ ክለቦች አንዱ ሲሆኑ በውሰት ወደ ጅማ ከተማ አምሮቶ ጥሩ አመት በማሳለፍ ከተመለሰው መጣባቸው ሙሉ ውጭ አስራ አንድ ተጨዋቾችን ከሀገር ውስጥና ከውጭ አስፈርሟል። ቢንያም ሐብታሙ ( ከድሬዳዋ) ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ ( ኢትዮ ኤሌክትሪክ ) ፣ አይናለም ኃይለ ( ደደቢት ) ፣ ራምኬል ሎክ ( ቅዱስ ጊዮርጊስ ) ፣ ብሩክ ግርማ ( ኢትዮጵያ ውሃ ስራ) እና አቤል ውዱ ( አውስኮድ ) ከሀገር ውስጥ የፈረሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በሚፈቅደው የውጭ ተጨዋቾች ቁጥር ገደብ መሰረት 5 ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡ እነሱም ሚካኤል ሳማኪ ( ግብ ጠባቂ/ ማሊ ) ፣ ክርስቶፎር አምሶቢ ( አጥቂ/ናይጄሪያ ) ፣ ሮበርት ሴንቴንጎ ( አጥቂ ዩጋንዳ ) ፣ ፊሊፕ ዳውዚ ( አጥቂ ናይጄርያ ) እና ያስር ሙገርዋ (አማካይ / ዩጋንዳ) ናቸው ።

ፋሲል ከተማ በኢትዮጵያ ከ20 አመት በታችም ሆነ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚወዳደሩ ቡድኖች ባይኖሩትም ከተስፋ ቡድኑ ያሬድ አበበ ፣ ዳንኤል ዘውዴ ፣ ናትናኤል ወርቁ ፣ አሀዱ አበራ እና ዮናስ ከተማ የተባሉ አምስት ተጨዋቾችን አሳድጓል።

ይህን ዝግጅት እስካጠናከርንበት ወቅት አብዱራህማን ሙባረክ በእረፍት ይስሐቅ መኩርያ በሀዘን ምክንያት ዝግጅት ያልጀመሩ ሲሆን ከሰሞኑ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ዝግጅት እንደሚጀምሩ ሰምተናል፡፡ የቀሩት የክለቡ ተጨዋቾች በሙሉ ግን ዝግጅታቸውን በጠንካራ ሁኔታ እየሰሩ እንደሆነ ተመልክተናል።

የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ በክለቡ ሙሉ ወጪ ለስልጠና ማቅናታቸውን ተከትሎ ቡድኑን እያዘጋጁ የሚገኙት ም/አሰልጣኙ ተገኝ እቁባይ ለሶከር ኢትዮዽያ በሰጡት አስተያየት የስብስብ ጥልቀት ችግር የ2009 ድክመታቸው እንደነበርና ለ2010 ለማሻሻል እንደሞከሩ ገልጸዋል፡፡
” ፋሲል አምና ውድድሩ ላይ ያሳየው ነገር በጣም ጥሩ ነው፡፡ ለፕሪምየር ሊጉ አዲስ ቢሆንም ልምድ ካላቸው ቡድኖች ባልተናነሰ ባለው ስብስብ ከደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን አብረውት ካደጉት የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ያም ቢሆን በቋሚነት የሚጫወቱትን ቀይረው የሚገቡ የተቀያሪ ተጫዋች ስብስቡ ብዛት አልነበረውም። ይህንን ምክንያት በማድረግ በየቦታው ክፍተቱን ይሞላሉ የተባሉ ተጨዋቾችን በዝውውሩ ተንቀሳቅሰን አምጥተናል። ሁሉም እኩል እና ተመጣጣኝ አቅም አላቸው፡፡ እንደምንጠቀመው የአጨዋወት ባህሪ በልምምድ እና በጨዋታ ወቅት እንደሚያሳዩት ወቅታዊ አቋም የምናሰልፍ ይሆናል። ዞሮ ዞሮ የስብስቡ መብዛት እንደምንጫወተው ጨዋታ ብዛት እና ከጉዳት ጋር ተያይዞ ለሚመጣው ችግር አማራጭ ስለሚያበዛ ስብስቡ መብዛቱ ጥሩ ነው” ብለዋል ።

በቢሸፍቱ ከተማ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ፋሲል ከተማ የቡድኑን ወቅታዊ አቋም ለመፈተሽ ይረዳው ዘንድ መስከረም አጋማሽ ላይ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው በደቡብ ካስትል ካፕ አልያም በአአ ሲቲ ካፕ ሊካፈል እንደሚችል ክለቡ እስካሁን ማረጋገጫ እንዳልሰጠ ለማወቅ ችለናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *