አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ስለ ነገው የኬንያ ጨዋታ ይናገራሉ

የኢትየጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ብድን ፈረንሳይ በ2018 ለምታስተናግደው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የአለም ዋንጫ ለማለፍ ነገ 10:00 ሰዓት በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም የማጣሪያ ጨዋታውን ከኬንያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ብድን ጋር ያደርጋል።

ብሔራዊ ቡድኑን ለመምራት የተመረጡት የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ዝግጅታቸውን ለማድረግ 31 ያክል ተጨዋቾችን በመጥራት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ እንዲሁም በጂምናዚየም ልምምዶችን ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ ጨዋታው ወደሚደረግበት ሀዋሳ ከተማ ያመሩ ሲሆን ከስብስባቸውም 6 ተጫዋቾችን በመቀነስ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዳቸውን እስኪያደርጉ ድረስ በ24 ተጫዋቾች ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ ስለ ዝግጅታቸው ፣ ስለ ቡድናቸው የጉዳት ዜና እና ስለ ጨዋታው ለሶከር ኢትየጵያ አስተያታቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ዝግጅታቸው

“ዝግጅታችን ጥሩ ነበር። ከነሃሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በቀን ሁለት ጊዜ ነበር ልምምዶችን ስናደርግ የነበረው። ጠዋት የአካል ብቃት ስራዎች ከሰዓት ደግሞ የሜዳ ላይ ስራወችን ስንሰራ ቆይተናል። ነገር ግን ከ ጳጉሜ 1 ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ልምምዶችን ስናደርግ የቆየነው። በአጠቃላይ ወደ 30 የሚጠጉ ልምምዶችን ስናደርግ ነበር።”

ስለተቀነሱ ተጨዋቾች

“ያሉኝ ተጨዋቾች ከእረፍት ስለመጡ መጀመሪያ ላይ ሰፋ ያለ የቡድን ስብስብ እንዲኖረን ፈልገን ነበር። ከነበሩኝ 30 ተጨዋቾች ውስጥ 6 ተጨዋቾችን በነበሩን የልምምድ ጊዜያት ቀንሰናል።”

ስለ ጉዳት
“ቡድኔ ውስጥ አሁን አንድ የጉዳት ዜና ብቻ ነው ያለው። ከደደቢት ከመረጥናት ትደግ ፍስሃ ውጪ ሁሉም የቡድኑ ተጨዋቾች በሙሉ ጤነኝነት ላይ ይገኛሉ። አጥቂያችን ትደግም በልምምድ ወቅት በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ለነገው ጨዋታ ብቁ አትሆንም እንጂ አልቀነስናትም። ለመልሱ ጨዋታ ምን አልባት የምትደርስልን ከሆነ የህክምና ባለሙያዎቻችን የሚሰጡንን ውጤት ተመልክተን ወደፊት አዳዲስ ነገሮችን የምንመለከት ይሆናል።”

ስለ ተጋጣሚያቸው ኬንያ

“ተጋጣሚያችን ሶስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን እንዳደረገ ሰምተናል። ነገር ግን ከመስማት እና መረጃዎችን ከማንበብ ውጪ በምስል ምንም አይነት መረጃ አላገኘንም። የነገው ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታችን እንደመሆኑ በ10 እና 15 ደቂቃዎች ውስጥ ቡድኑ ምን ይዞ እንደመጣ ለማየት እንሞክራለን።”

የወዳጅነት ጨዋታ ስላለማድረጋቸው

“የወዳጅነት ጨዋታ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም ባይኖርም ግን ያን ያህል ተፅእኖ ይፈጥርብናል ብዬ አላስብም። ባለን ጊዜ ከሀዋሳ የሲ ቡድን ጋር እና የእርስ በእርስ ጨዋታዎችን ለማድረግ ሞክረናል። ቡድኑን ከሚጠብቀው የማቀናጀት እና የማዋሃድ ስራ አንፃር ጠንከር ያሉ ጨዋታዎችን ብናገኝ ጥሩ ነበር፡፡

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታውን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን፡፡ ሆኖም ስለቡድኑ መረጃው ከሌለን ኬንያ ጋር እንደማድረጋችን እና የዝግጅት ጊዜ ተደማምሮ ጨዋታው እንደሚጠበቀው ሳቢ ላይሆን ይችላል፡፡ በእኛ በኩል በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል የመድረስ እቅድ ይዘን እንገባለን፡፡ “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *