ቻምፒየንስ ሊግ፡ ኤስፔራንስ እና ዩኤስኤም አልጀር ከሜዳቸው ውጪ ወሳኝ ውጤት አግኝተዋል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች አል አሃሊ በሜዳው ከኤስፔራንስ ጋር 2-2 ሲለያይ ወደ ሞዛምቢክ የተጓዘው ዩኤስኤም አልጀር በኩሉ በፌሮቫያሪዮ ቤይራ ጋር አቻ ተለያይቷል፡፡ የተመዘገቡት የአቻ ውጠየቶች በተለይ ኤስፔራንስ እና ዩኤስኤም አልጀርን ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ ያስችላቸዋል፡፡

በአሌክሳንደሪያ ከተማ በሚገኘው ቦርጅ አል አረብ ስታዲያም በተደረገው ጨዋታ አል አሃሊ ኤስፔራንስ ላይ ብልጫን ቢወስድም ማሸነፍ ግን ሳይችል ቀርቷል፡፡ አሃሊዎች ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆኑ አህመድ ኤል ሼይክ ከግቡ አንድ ሜትር ያገኘውን ቀላል እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በ11ኛው ደቂቃ ኤል ሼይክ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አብደላ ኤል ሰዒድ ከመረብ አገናኝቶ አሃሊን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላም አሃሊ ጫናውን ሲቀጥል ተደጋጋሚ ሙከራዎችንም የቱኒዚያ ተጋጣሚዉ ላይ ማድረግ ችሏል፡፡ ከ10 ደቂቃዎች በኃላ ተቀዛቅዘው የነበሩትን ኤስፔራንሶች ወደ ጨዋታ የተመለሱበትን ግብ ልማደኛው አጥቂ ጠሃ ያሲን ኬኔሲ ከማዕዘን ምት የተሻገረ ኳስ ፈርጃኒ ሳሲ በግንባሩ ሲገጭ ኬኔሲ ተንሸራቶ ግብ በማስቆጠር በአቻ ውጤት ለእረፍት አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ኤስፔራንስ ያልተጠበቀ መሪነተን የጨበጠበትን ግብ ጋሌን ቻላሊ በቅጣት ምት አስገኝቷል፡፡ በግምት ከ18 ሜትር ቻላሊ የመታው ቅጣት ምት በአሃሊው ግብ ጠባቂ ሻሪፍ ኤክራሚ ስህተት ግብ ሊሆን ችሏል፡፡ አሃሊዎች ግብ ካስተናገዱ በኃላ ተጋጣሚው ላይ ብልጫን መውሰድ ችሏል በ67ኛው ደቂቃ ዋሊድ አዛሮ የኤስፔራንሱ ግብ ጠባቂ ሞይዝ ቤን ሻሪፋ የተፋውን ኳስ በቅርብ ርቀት አግኝቶ ባስቆጠረው ግብ አሃሊ አቻ መለያይት ችሏል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረገው የመልስ ጨዋታ ኤስፔራንስ የማለፍ እድሉ ከአል አሃሊ የሰፋ ሆኗል፡፡

ቤይራ ላይ በተደረገ ጨዋታ ዩኤስኤም አልጀር ከፎሮቫያሪዮ ቤይራ ላይ የሙከራ የበላይነት ወስዶ 1-1 ጨዋታውን አጠናቅቋል፡፡ ቤይራ በሜዳው እንደመጫወቱ ለአልጄሪያው ክለብ ፈተና እንደሚሆን ቢገመትም ዩኤስኤም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ባለሜዳዎቹን ሲረብሽ ታይቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ዩኤስኤም ሁለት ያለቀላቸውን ሙከራች አምክኗል፡፡ ከእረፍት መልስ ዩኤስኤም በመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ ሲቀጥል በ63ኛው ደቂቃ ኦሳማ ዳርፋሎ በረጅሙ የተላከን ኳስ ከሁለት የቤይራ ተከላካዮች ነጥቆ በማለፍ ጭምር ኳስ እና መረብን አገናኝቶ የአልጀርሱን ክለብ መሪ አድርጓል፡፡ ግብ ካስተናገዱ በኃላ ቤይራዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ዩኤስኤሞች በጥብቅ መከላካል በሚገኟቸው የመልሶ ማጥቃት እድሎች ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ቶማስ ናይሬንዳ ያሻገረውን ኳስ ፋብሪስ ካንዳ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ በስታዲየሙ የተገኘውን ደጋፊ አስፈንድቋል፡፡ ውጤቱ ለዩኤስኤም አልጀር መልካም የሚባል ሲሆን የመጀመሪያ ተሳትፎውን በማድረግ ላይ የሚገኘው ቤይራ ወደ አልጀርስ ተጉዞ ማሸነፍ ይጠብቅበታል፡፡

ዛሬ ፕሪቶሪያ ላይ ኢትዮጵያዊው የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በሚመራው ጨዋታ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ዋይዳድ ካዛብላንካን ሲያስተናግድ አሌክሳንደሪያ ላይ አል አሃሊ ትሪፖሊ ከኤትዋል ደ ሳህል ይጫወታሉ፡፡

ውጤቶች
ክለብ ፌሬቫያሪዮ ደ ቤይራ 1-1 ዩኤስኤም አልጀር
አል አሃሊ 2-2 ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ

የእሁድ ጨዋታዎች
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሉካስ ማስተርፒስስ ሞሪፔ ስታዲየም)
አል አሃሊ ትሪፖሊ ከ ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *