​ሩሲያ 2018፡ ናይጄሪያ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፈች ቀዳሚዋ የአፍሪካ ሃገር ሆናለች

ለ2018ቱ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የምድብ አምስተኛ ጨዋታዎች ቅዳሜ ቀጥለው ሲደረጉ ናይጄሪያ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፈችበትን ትኬት ስትቆርጥ ቱኒዚያ ወደ ሩሲያ ለማምራት ከጫፍ ደርሳለች፡፡ በምሽቱ በተደረጉት ጨዋታዎች አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች፣ ቀይ ካርዶች፣ እና ሁለት ሃትሪኮች ታይተዋል፡፡

ምድብ አንድ

ቱኒዚያ በየሱፍ ሳክኒ ድንቅ ብቃት ታግዞ ጊኒን ከሜዳዋ ውጨ 4-1 በመርታት ወደ ሩሲያ ደጃፍ ስተትጠጋ ዲ.ሪ. ኮንጎ ሊቢያን 2-1 በማሸነፍ አሁንም የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ተስፋዋ እንዳይሟጠጥ አድርጋለች፡፡


ኮናክሬ ላይ ጊኒ በናቢ ኬይታ ግብ ቀዳሚ ብትሆንም በቱኒዚያ ከመሸነፍ ግን አልዳነችም፡፡ ሳክኒ የካርቴጅ ንስሮቹን በቅጣት ምት በመጀመሪያው አጋማሽ አቻ ሲያደርግ ከ18 ሜትር አክርሮ የመታው ኳስ ቱኒዚያን በ74ኛው ደቂቃ መሪ አድርጓል፡፡ መሃመድ አሚን ቤን አሞር እና ራሱ ሳክኒ ያስቆጠሯቸው ተጨማሪ ግቦችም ቱኒዚያ ከ2006 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ ከጫፍ አድርሷታል፡፡ በካታር የሚጫወተው የአጥቂ አማካዩ ሳክኒ ሐት-ትሪክ በመስራት በጨዋታው ላይ ደምቆ አምሽቷል፡፡ በአንፃሩ የጊኒን ግብ ያስገኘው አምበሉ ናቢ ኬይታ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ሞናስቴር ላይ ዲ.ሪ. ኮንጎ ሊቢያን 2-1 በማሸነፍ አሁንም የማለፍ ተስፋዋ እንዳይማጠጥ አድርጋለች፡፡ ልማደኛው ሴድሪክ ባካምቦ በ50ኛው ደቂቃ ኮንጎን መሪ ሲያደርግ አልሞታሲምቤላ አሊ ሊቢያ በ69ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓል፡፡ ፈርሚን ሙቤሌ በ75ኛው ደቂቃ ለኮንጎ ሶስት ነጥብ ያስገኘበትን ግብ በአደጋው ክልል ውስጥ ያገኘውን ኳስ ተጠቅሞ አስቆጥሯል፡፡

ቱኒዚያ ምድቡን በ13 ነጥብ ስትመራ ዲ.ሪ. ኮንጎ በ10 ትከተላለች፡፡ ጊኒ እና ሊቢያ ሶስት ነጥብ አላቸው፡፡ ቱኒዚያ በመጨረሻው ጨዋታ ከሊቢያ ጋር አቻ መለያየት ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ በቂዋ ነው፡፡


ምድብ ሁለት
ናይጄሪያ በአሌክስ ኢዮቢ ብቸኛ የሁለተኛ አጋማሽ ግብ ጠንካራ እንቅስቃሴ ያደረገችውን ዛምቢያ 1-0 በመርታት ወደ ዓለም ዋንጫው ማምራቷን አረጋግጣለች፡፡ ዛምቢያ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን በሆኑት የፊት መስመር ተሰላፊዎቿ የናይጄሪያን የተከላካይ ክፍል ስትረብሽ አምሽታለች፡፡ በሁለተኛው 45 ናይጄሪያ ይበልጥ ጫና ፈጥራ መጫወት ያቻለች ሲሆን ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የአርሰናሉ አጥቂ ኢዮቢ የድል ግቡን በ73ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡

በዚሁ ምድብ በተደረገ ጨዋታ ካሜሩን በሜዳዋ አልጄሪያን 2-0 ረታለች፡፡ ክሊንተን ንጂ እና ፍራንዝ ፓንጎፕ የማይበገሩት አናብስቶቹን ግቦች ሲያስገኙ አልጄሪያ አሁንም በመጥፎ የውጤት ጎዳና መጓዟን ቀጥላለች፡፡

ምድቡን ናይጄሪያ በ13 ነጥብ እየመራች ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፈች ሲሆን ዛምቢያ በ7፣ ካሜሮን በ6 እና አልጄሪ በ1 ነጥቦች ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡


ምድብ ሶስት

ሞሮኮ ጋቦንን በመርታት የምድቡን መሪነት ከኮትዲቯር ተረክባለች፡፡ የአምስተኛ ዙር የምድብ ጨዋታዎችን ተከትሎ ማሊ እና ጋቦን ከዓለም ዋንጫው ውጪ ሲሆኑ የማለፍ ፉክክር በኮትዲቯር እና ሞሮኮ መሃል ሆኗል፡፡

ካዛብላንካ ላይ በተደረገው ጨዋታ ሞሮኮ ካሊድ ቦታይብ በሰራው ሐት-ትሪክ ታግዛ ከጨዋታ የበላይነት ጋር 3-0 አሸንፋለች፡፡ በ38ኛው ደቂቃ ኒረዲን አምርባት ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ቦታይብ የአትላስ አንበሶቹን ቀዳሚ ሲያደርግ በ56ኛው ደቀቃ ሙባረክ ብሶፋ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ልዩነቱን አስፍቷል፡ በ72ኛው ደቂቃ የጋቦን ተከላካይ ንቃት ማነስ ተከትሎ የጨዋታው ኮከብ የነበረው ቦታይብ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ አስገኝቷል፡፡

ምድቡን ሞሮኮ በ9 ስትመራ አርብ እለት ከማሊ አቻ የተለያየችው ኮትዲቯር በ8 ትከተላለች ጋቦን በ5 እና ማሊ በ3 ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ በኮትዲቯር እና ሞሮኮ መካከል የሚደረገው የመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ከወዲሁ ቀልብን የሚስብ ሆኗል፡፡


ምድብ አራት
ደቡብ አፍሪካ የማለፍ ተስፋዋን ያለመለመችበትን ድል ቡርኪና ፋሶ ላይ ስትቀዳጅ ሴኔጋል ፕራያ ላይ ኬፕ ቨርዴን አሸንፋለች፡፡

ደቡብ አፍሪካ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ቡርኪና ፋሶን 3-1 ረታለች፡፡ ፐርሲ ታኦ፣ ቴምባ ዝዋኔ እና ሱቡሲሶ ቪላካዚ ባፋ ባፋን በመጀመሪያው አጋማሽ የ3-0 መሪነት ሲያስጨብጡ ከእረፍት መልስ ቡርኪና ፋሶዎች ጠንካራ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ በ67ኛው ደቂቃ የደቡብ አፍሪካው ተጫዋች ቦንጋኒ ዙንጉ አሊያን ትራኦሬን ለመደብደብ በመጋበዙ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ ትራኦሬ በግሩም ሁኔታ በቅጣት ምት ልዩነቱን ወደ ሁለት ያጠበበትን ግብ በ87ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡

ሴኔጋል በመጨረሻዎቹ 8 ደቂቃዎች ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች ከሜዳዋ ውጪ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችላለች፡፡ የቴራንጋ አንበሶቹ ኬፕ ቨርድን በዲያፍራ ሳኮ እና ቼክ ንዶዬ ግቦች 2-0 በማሸነፍ ምድቡን መምራት ጀምረዋል፡፡ ፊፋ የደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል ያደረጉትን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የጨዋታ ማጭበርበር ተፈፅሞበታል በማለት ጨዋታው የመራውን አርቢትር ጆሴፍ ላምፕቲን እድሜ ልክ ያገደ ሲሆን ጨዋታው በህዳር ወር እንዲደገም መወሰኑን ተከትሎ ሁለቱ ሃገራት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አላቸው፡፡

ምድቡን ሴኔጋል በ8 ነጥብ ስትመራ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርድ 6 ነጥብ አላቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ4 ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ትገኛለች፡፡


ምድብ አምስት
ዩጋንዳ እና ጋና ካምፓላ ላይ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ውጤቱ ከ2006 ጀምሮ የዓለም ዋንጫን ለተከታታይ ሶስት ግዜ የተሳተፈችው ጋናን ከማጣሪው ውጪ አድርጓል፡፡ በጨዋታው ላይ ራፋኤል ዱዋሜና ለጋና በባከነ ደቂቃ ግብ ቢያስቆጥርም አጥቂው ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ደቡብ አፍሪካዊው የመሃል ዳኛ ግቡን ሳያፀድቁ ቀርተዋል፡፡ ይህ አጋጣሚ ጋናዎችን ያላስደሰተ ሲሆን ሙሉ የቡድኑ አባላት ዳኛው ላይ ቅሬታቸው ሲያሰሙ ታይቷል፡፡ ዱዋሜና ያስቆጠራት ግብ በመልሶ ምልከታ ተጫዋቹ ከጨዋታው ውጪ አቋቋም ላይ እንዳልነበረ አሳይቷል፡፡ ከጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የጋና እግርኳስ ማህበር በአርቢትሩ ተበድያለው በማለት ቅሬታውን ለፊፋ አቅርቧል፡፡ ውጤቱ ለግብፅ መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ሲሆን እሁድ ኮንጎ ብራዛቪልን አሌክሳንደሪያ ላይ ማሸነፍ ከቻለች ከ1990 የዓለም ዋንጫ በኃላ የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ትኬቷን ትቆርጣለች፡፡

ምድቡን ግብፅ በ9 ስትመራ ዩጋንዳ በ8 ጋና በ6 ይከተላሉ፡፡ ኮንጎ በ1 ነጥብ የምድቡን መጨረሻ ደረጃን ይዛለች፡፡
የአርብ ውጤት

ማሊ 0-0 ኮትዲቯር

የቅዳሜ ጨዋታ

ደቡብ አፍሪካ 3-1 ቡርኪና ፋሶ

ዩጋንዳ 0-0 ጋና

ናይጄሪያ 1-0 ዛምቢያ

ካሜሮን 2-0 አልጄሪያ

ጊኒ 1-4 ቱኒዚያ

ሊቢያ 1-2 ዲ.ሪ. ኮንጎ

ኬፕ ቨርድ 0-2 ሴኔጋል

ሞሮኮ 3-0 ጋቦን

የእሁድ ጨዋታ (በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር)

2፡00 – ግብፅ ከ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *