የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዝግጅት – ሀላባ ከተማ

የሀላባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለ 2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ዝግጅቱን ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ በሀላባ ከተማ ዝግጅቱን ጀምሯል፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ምስረታቸው ረዘም ካሉት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀላባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከ50 አመታት በላይ እድሜ ቢኖረውም በርካታ ተጫዋቾችን ከማበርከት ባለፈ በትልቁ ሊግ ላይ ሳንመለከተው ቆይተናል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም በምድቡ ከፍተኛ ፉክክር አድርጎ በመጨረሻ ሳምንት የማለፍ እድሉን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡

ክለቡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ በቀድሞ የክለቡ ተጫዋቾች የተዋቀረ አዳዲስ ቴክኒክ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከሌላው ጊዜ ባለፈ ትኩረት ሰጥቶ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች እና ሀላባን በተለያዩ ጊዜያት ያሰለጠኑት ሚሊዮን አካሉ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩ ሲሆን እንዳለ አዱኛ እና ፋሪስ አወል በረዳትነት ይሰራሉ፡፡

በየአመቱ የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾች ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ የሚሰጠው ሀላባ ከተማ በአምናው የቡድኑ ጉዞ ወሳኝ የነበሩት ትዕግስቱ አበራ እና ዘካርያስ ፍቅሬን ወደ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ሸኝቶ 7 አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡ በሀላባ በክረምት ከሚደረገው አመታዊ ውድድር ላይ 2 እንዲሁም 5 ተጫዋቾችን ከታዳጊ ቡድኑ ለሙከራ አምጥቷል፡፡

አዳዲስ ፈራሚዎች

አዳዲስ ፈራሚዎች

ግብ ጠባቂ፡ ሶፎኒያስ ኑረዲን (ከሻሸመኔ ከተማ)

ተከላካዮች፡ ናትናኤል ጌታሁን (ደቡብ ፓሊስ)፣ ቴዎድሮስ ሀሙ (አርሲ ነገሌ)፣ እንየው ሙሉጌታ (ነገሌ ቦረና)

አማካዮች፡ ደረሰ ተሰማ (አርሲ ነገሌ)፣ ፉአድ ተማም (ወላይታ ድቻ)

አጥቂ፡ መሐመድ ናስር (ወልቂጤ ከተማ)

ከሀላባ የክረምት ውድድር የተገኙ፡ ተመስገን ደርቤ (አማካይ)፣ ቶፊቅ ሱልጣን (አማካይ)

አሰልጣኝ ሚልዮን አካሉ (መሀል) እና ረዳቶቻቸው

የቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑት ሚልዮን አካሉ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ አላማቸውን ለማሳካት የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ “ዝግጅታችን እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በመልካም ስሜት ካለፉት በርካታ ስተቶች ተምረን በቀጣይ አመት ደጋፊው ክለቡን በሊጉ እንዲመለከተው ነው እየሰራን ያለነው›› ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ አክለውም ” አሁን ገና ዝግጅት መጀመራችን ነው፡፡ ቡድኔን በወዳጅነት ጨዋታ በሚገባ እያየሁት ነው፡፡ በቀጣይ ቀናትም ከፕሪምየር ሊግ ካሉ ክለቦች ጋር ተጨማሪ ጨዋታዎችን ለማድረግ አስበናል፡፡ (ከወላይታ ድቻ ጋር ቅዳሜ ተጫውተዋል) ተደጋጋሚ ጨዋታን ማድረግ ለመጠናከር ይረዳናል፡፡ ይህም ደካማና ጠንካራ ጎናችንን ለማየት ይረዳናል፡፡›› ብለዋል፡፡

ከጥቅምት 11 ወደ 14 የተቀየረው እና በሆሳዕና ከተማ በሚዘጋጀው የደቡብ ክልል ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ዋንጫ ላይ ሀላባ ከተማ ይካፈላል፡፡ የከፍተኛ ሊግ ውድድር ጥቅምት 25 ሳጀመርም ከሜዳው ውጭ ድሬዳዋ ፓሊስን የሚገጥም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *