የእለቱ ዜናዎች: ጥቅምት 16 ቀን 2010

የስታድየም ስክሪን

ሞደርን ወርልድ ኃ.የተ.የግል ማህበር ከኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የአዲስ አበባ ስታድየም የውጤት ማሳያ ስክሪን በአዳዲስ ቴክሎኖጂ እና በዘመናዊ አቀራረብ ለመቀየር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ድርጅቱ ስክሪኑን  የመትከል ስራውን አጠናቆ በአሁን ሰአት በሙከራ ጊዜ ለይ የሚገኝ ሲሆን የፊታችን እሁድ በሚኖረው የአሸናፊ አሸናፊ ዋንጫ ላይ አገልግሎት እንደኒሰጥ ተገልፃል። ሙሉ ለሙሉ ስራው ሲጠናቀቅ በሰባት ካሜራ ሜዳ ላይ የሚደረጉትን የጨዋታ እንቅስቃሴ ፣ ውጤቶች ፣ የጨዋታ ደቂቃዎች እና ሌሎች የምስል ማሳያዎች እንደሚኖሩትም ሰምተናል።  


 ” ተጫዋች በመቅጣት የኢትዮዽያ እግርኳስ ችግር መፍትሔ አያገኝም “

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በጨዋታ ውጤት የማስቀየር ሙከራ ተሳትፈዋል ያላቸውን ተጫዋቾች ለመቅጣት መዘጋጀቱ መሰማቱን ተከትሎ የጅማ አባ ቡና ስራ አስኪያጅ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 
” የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን ሊወስን እያሰበ ያለውን ነገር እየሰማን እንገኛለን። ውሳኔው ምንም ይሁን  ምን ጅማ አባቡና እንደ ክለብ  ውሳኔውን ተከትሎ መግለጫ የምንሰጥበት ይሆናል። ሆኖም የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስፖርቱን ለመታደግ ህጉን የመተርጎም ኃላፊነት አለበት ብለን እያሰብን የጨዋታ ማጭበርበር ሙከራ አለ እየተባለ  ተጨዋቾችን መቅጣት በየትኛው ህግ ነው፡፡ ተጨዋቾቹም መብታቸውን መጠየቅ አለባቸው” ሲሉ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ይርጋለም ተናግረዋል፡፡

የደሞዝ ጥያቄ 

ጅማ አባ ቡና የሁለት ወር ደሞዝ አልከፈለንም በማለት በ2009 ለክለቡ የተጫወቱት ኄኖክ ካሳሁን ፣ ሲሳይ ባንጫ ፣ ኄኖክ ኢሳይያስ ፣ አሜ መሐመድ ለኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያቀረቡትን ጥያቄ ተመልክቶ ጅማ አባቡና በአምስት ቀናት ውስጥ ለተጨዋቾቹ ገቢ እንዲያደርግ ተወሰኗል፡፡ ይህን ተከትሎ ጅማ አባቡና በዚህ ሳምንት ደሞዛቸውን እንደሚከፍልና እስካሁንም የዘገየው ክለቡ ገንዘብ የሚያገኝበት መንገድ መሆኑን ተገልጿል። 


ቅጣት

ሀዋሳ ከተማ ታፈሰ ሰለሞንን ከፍተኛ የዲሲፒሊን ቅጣት ሊቀጣው እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል ። በተደጋጋሚ ከክለቡ ህግ ውጭ ያልተገባ ባህሪ እያሳየ መገኘቱ ቅጣቱ መነሻ እንደሚሆን ሲገለፅ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ልምምድ እንዳልሰራ ሰምተናል። ታፈሰ ሰለሞን ከዚህ ቀደም በሚፈፅማቸው ያልተገባ ባህሪ ምክንያት ክለቡ ሀዋሳ ቅጣት መቅጣቱ የሚታወስ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ መቀነሳቸውም ይታወሳል ።   


ኢትዮጵያዊያን በውጪ

በሰባተኛ ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ስሞሃ ሳይጠበቅ በሜዳው በታላል ኤል ጋይሽ 1-0 ተሸንፏል፡፡ በአሌክሳንደሪያ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኡመድ ኡኩሪ ለ73 ደቂቃዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ በውድድር ዓመቱ አንድ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ኡመድ በዋሊድ ሃሰን ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ በጨዋታው ኤል ጋይሾች በመልሶ ማጥቃት እና ይዘውት በገቡት የመከለካል ስትራቴጂ ፍሬ አፍርቶ ስሞሃን ማሸነፍ ችለዋል፡፡ የድል ግቡን በኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በ2009 የውድድር ዓመት የኡመድ የአጥቂ አጣማሪ የነበረው ሳላህ አሚን የግራ መስመር ተከላካዩ አሰም ሳላህ ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል፡፡ ስሞሃ ከሳምንት በፊት ሃያሉን ዛማሌክን 3-0 ማሸነፉን ተከትሎ የተመዘገበው ውጤት አስገራሚ ነው፡፡ አሰልጣኝ ፍራንቼስክ ስትራካ የሚከተሉት በተወሰኑ ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ ታክቲክ ቡድኑ አምና ሲጠቀምበት ከነበረው ጋር መለያየቱ ተጫዋቾቹ በፍጥነት እንዳይላመዱት አድርጓቸዋል፡፡ ስሞሃ በ12 ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ በ3ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ 

የሽመልስ በቀለው ፔትሮጀት ቅዳሜ ከሰዓት 9፡45 ላይ ኤል ናስርን በአስ ስዌዝ ስታዲየም ያስተናገዳል፡፡


ባምላክ ተሰማ 
የካፍ ቶታል የቻንፒየንስ ሊግ የመጀመርያ ጨዋታን በዋና ዳኝነት እንዲመራ የተመረጠው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ዛሬ ማምሻውን ወደ ግብፅ የሚያመራ ሲሆን ጠዋት ረፋድ ላይ ልምምዱን ሲሰራ አግኝተነው እንደተናገረው በመመረጡ በጣም እንደተደሰተ ገልጿል፡፡  በቀጣይም የአፍሪካ ምድብ የአለም ዋንጫ ወሳኝ የማጣርያ ጨዋታ ሊመራ እንደሚችል ገልፆ ቅዳሜ ከሚኖረው የፍፃሜ ጨዋታ መልስ ሰፊ ቃለ ምልልስ ለሶከር ኢትዮዽያ እንደሚሰጥ ተናግሯል።
የአል አህሊ እና የዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ ጨዋታ ቅዳሜ ምሽት የሚደረግ ይሆናል፡፡

ነቀምት ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጠረ

ንግድ ባንክን በመተካት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ሊመተስ እንደሚችል የተነገረው ነቀምት ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡ የቀድሞው የሲዳማ ቡና ምክትል አሰልጣኝ እና የደቡብ ፖሊስ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ቾምቤ ገብረህይወት ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡


ስፖርታዊ ጨዋነት 

የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን “ቅድሚያ  ለስፖርታዊ ጨዋነት” በሚል መርህ የስፖርታዊ ጨዋነት የግንዛቤ ማስጨበጫ በሀዋሳ ኃይሌ ሪዞርት አርብ እና ቅደዳሜ ያከናውናል፡፡
በደቡብ ክልል ባሉ የፕሪሚየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ፣  አንደኛ ሊግ፣ የሴቶች እና ታዳጊ የእግር ኳስ ክለቦች የክለብ የቦርድ አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣  የየክለቡ አምበሎች፣  የክለብ ስራ አስኪያጆች፣  የደጋፊ ማህበር ፕሬዝዳንቶችና ጥቂት የደጋፊ ተወካዮች እንዲሁም በአጠቃላይ በእግር ኳሱ ዙርያ ያሉ አካላትም በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ተጋባዥ ሆነዋል፡፡
ስልጠናው በዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ እና የሳይኮሎጂ ምሁራን እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽንና በክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን በተወከሉ ባለሙያወች እንደሚሰጥ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡

የሲዳማ ቡና ሴቶች ቡድን እስካሁን ዝግጅት አልጀመረም

አምና ዘግይቶ ወደ ውደድድር የገባውና ከምድብ ለ 5ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ በአንደኛ ዲቪዝዮን ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው የሲዳማ ቡና የሴቶች ቡድን ዘንድሮም እንደ አምናው ሁሉ ዝግጅት አልጀመረም፡፡ 

የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ክለቡ ለስቶች ቡድኑ ትኩረት እየነፈገ እንደሆነ ገልጿል፡፡ “ክለቡ አዳዲስ ተጫዋቾችን አላስፈረመም፡፡ በአንፃሩ በርካታ ተጫዋቾችን በሌሎች ክለቦች ተነጥቀናል፡፡ በእኔም ሆነ ባሉት ተጫዋቾች መካከል ችግሮች የሉም፡፡ በክለቡ በኩል ግን በዚህ ቀን ዝግጅት ጀምሩ የሚል ነገር አልቀረበልንም፡፡ ይህ ግን የተጫዋቾች አልያም የኔም ችግር አይሆንም፡፡ በሊጉ ውጤት ቢጠፋም ተጠያቂ አንሆንም፡፡” ሲሉ አሰልጣኙ ገልፀዋል፡፡

የፎቶ አውደ ርዕይ ነገ ይጀመራል

በጋዜጠኛ ታሪኬ ቀጭኔ ለ2ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የቀደምት ስፖርተኞችን ፎቶ የሚያሳይ አውደ ርዕይ ነገ በቂርቆስ ቤተክርስቲያን አዳራሽ ይጀመራል፡፡ እስከ እሁድ ድረስም ይቀጥላል፡፡ በአውደ ርዕዩም ከዚህ ቀደም የተጎበኙ ፎቶዎችን ጨምሮ አዳዲስ ፎቶዎች መካተታቸውን ጋዜጠኛ ታሪኬ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡


የአፍሪካ ዜናዎች

ኬንያ

የኬንያ ፕሪምየር ሊግ የ31ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሃገሪቱ በሚደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ምክንያት ተራዝመዋል፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ሊደረጉ የነበሩት ጨዋታዎች የተራዘሙት በኬንያ የሚደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ውጥረት መንገሱን ተከትሎ ነው፡፡ በአንዳንድ አከባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያቱም ሊጉ ለህዳር 1/2017 ሲዛወሩ የ32ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ህዳር 14 እንደሚደረጉ ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል፡፡ ይህንን ተከትሎ በህዳር 11 ኬንያ ለሴካፋ ዋንጫ መዘጋጇ እንዲረዳት ከሩዋንዳ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ላይ እክል እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡ የኬንያ እግርኳስ ማህበር ሁሉንም የፊፋ ካለንደር ላይ ያሉ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ግዜያት በመጠቀም የወዳጅነት ጨዋታ እያደረገ ሲሆን የሩዋንዳንም ጨዋታ የመዝለል ምንም ሃሳብ የለውም፡፡ የኬንያ ስፖርትፔሳ ሊግን ጎር ማሂያ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ሴራሊዮን 

የሴራ ሊዮን እግርኳስ ማህበር ፕሬዝደንት ኢሻ ጆንሰን እና ዋና ፀሃፊው ክርስቶፈር ካማራ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ከእግርኳስ ማህበሩ ስልጣን እንደተነሱ ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡ ጆንሰን እና ካማራ የስራ አስፈፃሚ አባላት ድጋፍ ያገኙ ሲሆን በወንጀል የተጠረጠሩ ማንኛውም የሴራ ሊዮን ባለስልጣን በሃገሪቱ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ህግ መሰረት በስልጣን ላይ መቆየት አይችልም፡፡ በዚህ ህግ የተነሰ ሁለቱ ቁልፍ የእግርኳስ ማህበሩ መሪዎች ከስልጣናቸው ተነስተዋል፡፡ ሁለቱም ሰኞ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሲሆን በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ አንዳልሆኑ ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡ የእግርኳስ ማህበሩ ምክትል ፕሬዝደንት ብሪማ ማዞላ ካማራ በግዜያዊነት ፕሬዝደንት እንዲሁም አብዱል ራህማን በዋና ፀሃፊነት ተሹመዋል፡፡ ኢሻ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ታደሰ በምትገኝበት የካፍ የሴቶች እግርኳስ አዘጋጅ ቋሚ ኮሚቴ መሪ መሆኗ ይታወቃል፡፡

ቱኒዚያ 

ከካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በከባድ ሽንፈት ከግማሽ ፍፃሜ የወደቀው የቱኒዚያው ኤትዋል ደ ሳህል የቡድኑን ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ሁበርት ቬሉድን ሲያሰናብት የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ዚያድ ጃዚሪ በገዛ ፍቃዱ ከክለቡ ለቋል፡፡ በአል አሃሊ ባሳለፍነው ሳምንት 6-2 የተሸነፈው የሶሱ ሃያል ክለብ ለውጦችን እንደሚያደርግ ሲጠበቅ ነበር፡፡ የቀድሞ የቲፒ ማዜምቤ እና ዩኤስኤም አልጀር አሰልጣኝ ቬሉድ ከክለቡ ጋር ዓመት ሳይሞላቸው ተሰናብተዋል፡፡ የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ጃዚሪ ደግሞ ስራውን ከዚህ በኃላ ማከናወን እንደማይችል በመግለፅ እረቡ ከስራው በገዛ ፍቃዱ ተነስቷል፡፡ ጃዚሪ በ2004 ቱኒዚያ የአፍሪካ ቻምፒዮን ስትሆን እና ወደ 2006ቱ የዓለም ዋንጫ ስታመራ ቁልፍ ሚናን የተወጣ የፊት መስመር ተጫዋች ነበር፡፡

ግብጽ

የግብፁ ክለብ አል አሃሊ እና ማሊያዊው አጥቂ ሱሌማን ኩሊባሊ ውዝግብ አሁንም መቀጠሉን መቀመጫውን ካይሮ ያደረገው የግብፅ እግርኳስ ድረ-ገፅ ኪንግፉት ዘግቧል፡፡ ሱሌማን ያለክለቡ ፍቃድ ከግብፅ ከወጣ በኃላ ደብዛው በመጥፋቱ አል አሃሊ ተጫዋቹን በፊፋ ፊት ከሷል፡፡ ሱሌማን ፊፋን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን የአእምሮ መረበሽ በሽታ ተጠቂ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ አሃሊ በዚህ አይስማማም፡፡ የአሃሊ የህግ አማካሪ ሀልሚ አብደልራዛቅ ተጫዋቹ ከካይሮው ክለብ ጋር ውል ሲገባ ስለዚህ ጉዳይ አለማንሳቱን አስታውሰዋል፡፡ ሱሌማን በተጨማሪም የአሃሊ አሰልጣኝ ሆሳም ኤል ባድሪ ግብ ከተቆጠረ በኃላ የእስልምና ተከታይ ተጫዋቾች እንደሚያደርጉት እንድሰግድ አስገድደውኛል የሚለውንም ቅሬታ ሀልሚ ከእውነት የራቀ ብለውታል፡፡ “አል አሃሊ ከሌሎች ሃገራት የተለያየ እምነት ተከታይ የሆኑ ተጫዋቾች ያስፈርማል፡፡ አንድም ግዜ የተለየ ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን ተጫዋቾች እንዲፈፅሙ አድርጎ አያውቅም ሲሉ ክለባቸውን ተከላክለዋል፡፡”

ደቡብ አፍሪካ

ሲፍዌ ሻባላላ ለደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ከአራት ዓመታት በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ መመረጡ ታውቋል፡፡ አሰልጣኝ ስትዋርት ባክተር ከሴኔጋል ጋር ከፊታቸው ላለባቸው ሁለት ወሳኝ የደርሶ መልስ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ የቡድን ስብስባቸውን ይፋ ሲያደርጉ የ33 ዓመቱ የመስመር ተጫዋች ባልተጠበቀ መልኩ የተካተተው፡፡ ሴኔጋል ወደ ሩሲያ የዓለም ዋንጫ ለማምራት ሁለት ነጥብ ብቻ ሲያስፈልጋት ደቡብ አፍሪካ ለማለፍ ሁለቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ አለባት፡፡ 

ማሊ 

ማሊ ከፊፋ የዓለም 17 ዓመት በታች ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ በስፔን 3-1 ተሸንፋ ወድቃለች፡፡ ማሊ በግማሽ ፍፃሜው የቀረችው ብቸኛው የአፍሪካ ሃገር የነበረች ቢሆንም ከስፔን ጋር በነበራት ጨዋታ ግን ማሸነፍ ሳትችል ቀርታለች፡፡ አቤል ሩይዝ (2) እና ፈራን ቶሬስ የድል ግቦቹን ሲስቆጥሩ ማሊን ከመሸነፍ ያላዳነች ግብ ላሳና ንዳዬ አስገኝቷል፡፡ ጃፓናዊው የመሃል ዳኛ የማሊው ቼክ ዱኮር ከ30 ሜትር ያስቆጠረውን ግሩም ግብ ኳስ ከመስመር አላለፈች በሚል ሳያፀድቁ ቀርተዋል፡፡ በመልሶ ምልከታ ግን ኳስ መስመር ማለፉ ታይቷል፡፡ ማሊ በደረጃ ከብራዚል ስትጫወት ስፔን እና እንግሊዝ በፍፃሜው ይገናኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *