ሰበር ዜና፡ ካፍ ለኢትዮጵያ ወደ ቻን የመመለስ ሁለተኛ እድልን ሰጠ

ሞሮኮ በጥር 2018 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ያለፉ 16 ሃገራት አስቀድመው ቢታወቁም የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የግብፅን አለመካፈል ተከትሎ የምስራቅ እና መካከኛው አፍሪካ ዞን አንድ ተጨማሪ ሃገር ለውድድሩ እንዲያልፍ ወስኗል፡፡ በመጨረሻው የማጣሪያ ዙር የወደቁት ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የደርሶ መልስ ጨዋታ አድርገው ወደ ሞሮኮ እንዲያመሩም ዳግመኛ እድል ሰጥቷቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሱዳን፣ ሩዋንዳ ደግሞ በዩጋንዳ ተሸንፈው ነው ከውድድሩ ውጪ የሆኑት፡፡ ግብፅ የሊግ ውድድሯን ላለሟቋረጥ እና ለዋናው ብሄራዊ ቡድኗ የዓለም ዋንጫ መዘጋጃ ሰፋ ያለ ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከቻን እራሷን ማግለሏን ተክተሎ ከሰሜን ዞን አልጄሪያ ትሳተፋለች ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ሳይሆን በመቅረቱ እድሉ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ዞሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት የካፍ የሚዲያ ኃላፊ ጁኒየር ቢኒያም እድሉ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተሰጠበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡  “መሆን የነበረበት ከሰሜን ዞን ያለ ቡድን ነበር፡፡ ደንቡም ይህንን ይደግፋል፡፡ ነገር ግን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ እንዲጫወቱ ወስኗል፡፡” ብለዋል፡፡ ጁኒየር ለምን የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ውሳኔውን ለመወሰን እንደቻለ ከመጥቀስ ግን ተቆጥቧል፡፡

ኢትዮጵያ ሩዋንዳን ጥቅምት 26 አዲስ አበባ ላይ ስታስተናግድ የመልስ ጨዋታው ከሳምንት በኃላ ህዳር 3 ኪጋሊ እንደሚጫወቱ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል፡፡ ኢትዮጵያ በ2014 ለቻን ለመጀመሪያ ግዜ ስታልፍ ሩዋንዳን በመለያ ምት አሸንፋ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ጀርመናዊው የአማቩቢዎቹ አሰልጣኝ አንቶኒ ሄይ ለዝግጀት 24 ተጫዋቾችን ከወዲሁ የጠሩ ሲሆን እሁድ ዝግጅት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ሁኔታ ግን እስካሁን አልታወቀም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *