“ቅድሚያ ለስፖርታዊ ጨዋነት” የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ውይይት መድረክ በሀዋሳ ተካሄደ

“ቅድሚያ ለስፖርታዊ ጨዋነት” በሚል መርህ በሀዋሳ የስፖርታዊ ጨዋነት ግንዛቤ ማስጨበጫ እና ውይይት መድረክ በደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እና በክልሉ እግርኳስ ፌድሬሽን ትብብር አርብ በኃይሌ ሪዞርት ተካሂዷል፡፡

መድረኩን ለማዘጋጀት የታሰበው ጥቅምት 17 እና 18 ቢሆንም አርብ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ምሸቱ 3:00 ድረስ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ተጠናቋል፡፡ በውይይቱም የዞን እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ የክለብ አመራሮች፣ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪዎች፣ የደጋፊ ተወካዮች እና ከደቡብ ክልል የተወጣጡ በእግር ኳሱ እና እግር ኳሱ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላት በአጠቃላይ ከ450 በላይ ተሳታፊዎችን ተገኝተዋል፡፡

መድረኩን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሲሆን አቶ ገልገሎ ገዛኸኝ  (የስፖርት ሳይንስ ምሁር እና የቢሮው ስፖርት ዘርፍ ኃላፊ) ለእግር ኳሱ መቀጨጭ አንዱ መንስኤ በሆነው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ላይ የተሰራ ጥናት የያዘ ሰነድ ለታዳሚው አብራርተዋል፡፡

በሰነዱ ላይ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ተብለው በርካታ ጉዳዮች ተጠቁመዋል፡፡ የክለብ አመራሮች ላልተገባ ጥቅም መሮጥ በተለይ ዳኞችን እና ኮሚሸነሮችን በጥቅም የመደልደል፣ አሰልጣኞች ተጫዋቾችን ለፀብ ማነሳሳት፣ የቡድን መሪዎች ቡድን ከመምራት ተግባራቸው ውጪ በማይመለከታቸው ጉዳዮች በመግባት ችግር የመፍጠር፣ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የጠበኝነት ባህሪን ለማሳየት መነሳሳት፣ የተደራጀ የአደጋገፍ ስልት በደጋፊው እና በደጋፊዎች ማህበር ላይ ያለመታየት፣ ብሔርን እየጠሩ አሰልጣኝ እና ተጫዋች መሳደብ፣ የፀጥታ አካላት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ለከተማቸው ክለብ አልያም ለሚደግፉት ክለብ መወገን፣ የሚዲያ ተቋሞች ሚዛናዊ ያልሆነ እና አድሎ የበዛበት ዘገባ መዘገብ በሀገሪቱ የሚታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡

ከጥናት ማብራርያው በኋላ በተደረገው ውይይት በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን የችግሩ ስር መስደድ እና ሊወሰዱ የሚገባቸው መፍትሄዎች ተጠቁመዋል፡፡ ከመድረኩም ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *